ስለ ኢትዮጵያ የአስተዳደር ህግ ብሎም ውልደቱ፣ አነሳሱና ታሪካዊ ዕድገቱ ለመጻፍ ብዕሩን የሚያሾል ጸሐፊ ጭብጥ እንዳጣ የልብለወለድ ደራሲ ከየት ልጀምር? በሚል ጭንቀት ተውጦ ጣራ ላይ ማፍጠጥ አይቀርለትም፡፡ ስራውን ፈታኝ የሚያደርገው በህዝብ አስተዳደር እና በአስተዳደር ህግ ላይ የተጻፉ የታሪክ መዛግብት፣ የምርምር ጽሑፎችና መጻህፍት አለመኖር ብቻ አይደለም፡፡ በእርግጥ ለጀማሪ አጥኚ ይህ በራሱ ራስ ምታት ነው፡፡ ከመነሻ ምንጭ እጥረት ባሻገር ሌሎች ዐቢይ ምክንያቶች የአገሪቱን የአስተዳደር ህግ ጉዞ መዘገብ አድካሚ ያደርጉታል፡፡ ለመጥቀስ ያህል፤
- የጥናት አድማሱ ወጥነት እና ትኩረት ማጣት[1]
- የዲሞክራሲና ህገ መንግስታዊ ዳራው[2]
- የፖለቲካና አ[3]ስተዳደር መደበላለቅ
- የህግ አውጭውና የፍርድ ቤቶች ሚና ማነስ[4]
ባደጉት አገራት የአስተዳደር ህግ ዕድገት ጥርት ባለ መልኩ ወጥነትና ስርዓት እየያዘ ራሱን የቻለ የህግ ክፍል ሆኖ ብቅ ማለት የጀመረው የዘመናው የአስተዳደር (Administrative State) ወይም የማህበራዊ ዋስትና መንግስት (Welfare State) መከሰት ተከትሎ ስለመሆኑ ብዙዎች የመስኩ አጥኚዎች ይስማሙበታል፡፡ በተመሳሳይ ቅኝት ስለ አገራችን አስተዳደር ህግ ታሪካዊ ገጽታዎችና መገለጫዎች ከዘመናዊ አስተዳደር ማቆጥቆጥ ጋር አስታኮ አጠቃላይ ገለጻ መስጠት ይቻላል፡፡
በርካታ የአገራችን ሆኑ የውጭ አገር ታሪክ ጸሐፊዎች በአገራችን ዘመናዊ አስተዳደር የተተከለው የኃይለስላሴ ዙፋን ላይ መውጣት ተከትሎ በነበሩት ዓመታት ውስጥ እንደሆነ ይስማሙበታል፡፡ በተለይም ከኢጣሊያ ወረራ ማብቃትና የንጉሱ ዙፋን መልሶ መረከብ አንስቶ ዘመናዊ አስተዳደር ፈጣን ለውጦች አሳይቷል፡፡
ስለ ኢትዮጵያ የመንግስት አስተዳደር እና አስተዳደር ሲመራበት ስለነበረው ህግ ሲነሳ የአጼ ቴዎድሮስ ውጥን እና ጥረት ሳይጠቀስ አይታለፍም፡፡ አጼ ቴዎድሮስ ብሔራዊ ጦር ለማደራጀት፣ የቤተክስርስትያን የመሬት ይዞታ ለመቆጣጠር፣ የአካባቢ የጦር አበጋዞች በማዕከላዊ መንግስት ስር ለማዋቀር እንዲሁም የመንገድ ግንባታና ሌሎች ማህበራዊ አገልግሎቶች ለመዘርጋት ያደረጓቸው ጥረቶች ለቀጣይ ነገስታት መሰረት ጥለዋል፡፡ ጠንካራ ማዕከላዊ መንግስት ለማቆም እና ዘመናዊ አስተዳደር ለመትከል የነበራቸውን ህልም፣ ውጥን እና ፖሊሲ እንዲሁም እነዚህን ለመተግበር የወሰዷቸው ስር ነቀል እርምጃዎች የለውጥና የስልጣኔ በር ከፍተዋል፡፡
የኢትዮጵያ የአስተዳደር ህግ ውልደት ከቴዎድሮስ ይጀምራል፡፡ አስተዳደራዊ ብልሹነት እንዲቀረፍና ሹመኞች በህዝብ አገልጋይነታቸው በደል እንዳይፈጽሙ በጊዜው ሲያደርጉት የነበረው ክትትል እና የስልጣን ቁጥጥር በኢትዮጵያ የታሪክ መጻህፍት ጎልቶ ባይወጣም በአንዳንድ ጽሁፎች ተዘግቦ ይገኛል፡፡ በደርግ ወታደራዊ መንግስት ልዩ ፍርድ ቤት ይዘጋጅ የነበረው ሕግና ፍትሕ መጽሔት በመጋቢት 1987 እትሙ አጼ ቴዎድሮስ ሙስና እና የአስተዳደር ብልሹነት እንዲወገድ ሲያደርጉት የነበረውን ተጋድሎ ሌላ ምንጭ ጠቅሶ እንደሚከተለው ዘግቦታል፡፡[5]
ቴዎድሮስ ወዘልውጥ በመሆንና አልባሌ ልብስ በመልበስ በመንግስቱ ውስጥ ያለው የአስተዳደር መበላሸት መቆጣጠር፣ ጉቦኞች ሹማምንቶቻቸውን መከታተልና ማጋለጥ ያዘውትሩ ነበር፡፡ በሕዝብ ችግር የጨከኑትን፣ ለግል ጥቅማቸው ሲሉ የመንግስቱን ስራ የሚበድሉትንና ኅብረተሰቡን ያጉላሉትን ሹማምንት ከስልጣን ወንበራቸው ገልብጠዋል፡፡ አባ ታጠቅ ስልጣን በጨበጡ በመጀመሪያዎቹ ዓመታት ውስጥ የጯሂ ጠባቂ (የህዝብ ዕንባ ጠባቂ) ሹማቸው ጉቦ መቀበሉን በማወቃቸውና ራሳቸውም ሲቀበል በማየታቸው በአደባባይ አጋልጠው ሽረውታል፡፡…የጯሂ ጠባቂነቱንም ሥራ ራሳቸው ይዘዋል፡፡
አጼ ቴዎድሮስ የመንግስት ስልጣን በህግና በስርዓት እንዲገራ የነበራቸው ቆራጥ አቋም በታሪክ በተዘገቡ ጥቂት የጊዜው ፍርዶች ላይም ይታያል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንደኛው በጳውሎስ ኞኞ አጤ ቴዎድሮስ መጽሐፍ ላይ እንደሚከተለው ተዘግቧል፡፡[6]
ቴዎድሮስ ጋይንት ላይ ሰፍረው ሳለ ወታደሮቻቸውን በባላገሩ ላይ ተሰሪ አስገቡ፡፡ ባለገሩ እንዲቀልብ በየቤቱ ማስገባት ማለት ነው፡፡ ተሰሪ ከገቡት ወታደሮች መሀል አንዱ ወታደር አንዱን ባላገር ገደለው፡፡ የሟች ወገንም ከቴዎድሮስ ዘንድ መጥቶ አመለከተ፡፡ ቴዎድሮስም ወታደራቸውን ሁሉ አፈርሳታ አስቀምጠው ገዳዩን አውጣ ብለው ያዙ፡፡ ወታደሩም በመላው አድሞ ገዳዩን አላየንም እያለ በቄስ እየተገዘተ ወጣ፡፡ የሟች ገዳይ ወታደር በመጥፋቱ ቴዎድሮስ ተናደው ‘ወታደር ብላ፤ ባላገር አብላ ያልሁ እኔ ነኝ፡፡ ደመኛህም እኔ ነኝና እኔን ግደል’ ብለው ተነስተው ለከሳሹ ነገሩት፡፡ ከሳሹም ‘እኔ ንጉስ መግደል አይቻለኝም’ አለ፡፡ ቴዎድሮስም ደም በከንቱ አይቀርም ብለው ለሟቹ ወገን የደም ገንዘብ ዋጋ ሰጥተው ሸኙት፡፡
በሌላ ፍርድ ላይ እንዲሁ ለሁለት ወታደሮቻቸው የሰጡት እርስ በርሱ የሚጋጭ ትዕዛዝ የአንደኛውን ወታደር ሞት በማስከተሉ ለሞቱ መከሰት ተጠያቂ ተደርገው ስለተፈረደባቸው በዚያ ንጉስ በማይከሰስበት፤ ሰማይ በማይታረስበት ዘመን ቅጣታቸውን ተቀብለው ፍርዱን ፈጽመዋል፡፡ ታሪኩ በአጭሩ እንደዚህ ነው፡፡
ቴዎድሮስ አንዱን ወታደራቸውን ‘በፍርቃ በር በኩል እርጉዝ ሴት እንኳን ብትሆን እንዳታልፍ ጠንክረህ ጠብቅ’ ብለው ካዘዙት በኋላ በሌላ ቀን ደግሞ ሌላውን ወታደር ጠርተው ‘ፈረስ እያለዋወጥህ ይህን ወረቀት የጁ ሰጥተህ በአስቸኳይ በስድስት ቀን ውስጥ ተመልሰህ እንድትመጣ’ ብለው ሲልኩት እየጋለበ ሄዶ ፍርቃ በር ላይ ሲደርስ ጠብቅ ከተባለው ወታደር ጋር ‘አልፋለው! አታልፍም!’ እሰጥ አገባ ገጥሙ፡፡ በግዴታ ለማለፍ መንገድ ሲጀምር ዘበኛው ተኩሶ ገደለው፡፡ የንጉስ ትዕዛዝ ሲፈጽም የነበረ የንጉስ መልዕክተኛ በዚህ መልኩ መገደሉ ያንገበገባቸው የሟች ወገኖች ገዳዩን በመክሰስ ከቴዎድሮስ ዘንድ አቀረቡት፡፡ ቴዎድሮስም ችሎት አስችለው ፍርድ እንዲፈረድ አደረጉ፡፡
በችሎት የተቀመጠው ፈራጅ ሁሉ እየተነሳ ገዳዩን ‘በደለኛ ነህ እምቢ አልፋለው ቢልህስ ለንጉስ ታሰማ ነበር እንጂ ራስህ ፈርደህ እንዴት የንጉስ መልዕክተኛ ትገድላለህ? አሁንም ስትሞት ይታየናል’ እያሉ ፈረዱ፡፡ አንደኛው ፈራጅ ግን ከተቀመጡበት ተነስተው ከሌሎቹ ፈራጆች በመለየት ሁለት ተቃራኒ ንጉሳዊ ትዕዛዝ መስጠት አግባብ ስላልሆነ ጥፋቱ የሚመለከተው ንጉሠ ነገሥቱን እንደሆነ ከተናገሩ በኋላ ‘ነገር ግን እሳቸው ብርሀን ስለሆኑ ምን ይደረግ?’ በማለት የፍርድ ሀሳባቸውን አሳርገው ተቀመጡ፡፡ አጤ ቴዎድሮስም ይህን የልዩነት የፍርድ ሀሳብ አድንቀው ከተቀመጡበት ተነስተው በተከሳሹ ወታደር ቦታ ወርደው ቆሙ፡፡ በመጨረሻም ፈራጆች በፈረዱት መሰረት በጊዜው የሚከፈለውን የደም ዋጋ አጠፌታውን ብር 500 ከፍለው ጉዳዩ በስምምነት አለቀ፡፡[7]
እነዚህ ሁለት ፍርዶች በጊዜው የነበረውን አጠቃላይ የፍትሕና የዳኝነት ስርዓት እንደማያንጸባርቁ ምክንያታዊ ጥርጣሬ ሊያስነሳ ይችላል፡፡ ሆኖም አንድ መሰረታዊ ነጥብ በጥንቃቄ መታየት አለበት፡፡ ፍርዶቹ የተሰጡበት ዘመን ፍጹማዊ በነበረው የንጉስ ስልጣን ላይ ገደብ እና ተጠያቂነት ሰማይን የማረስ ያክል በተግባር ሊታይ ቀርቶ ከነጭራሹ አይታሰብም፡፡ እውነቱን ለመናገር እስከአሁኑ ጊዜ ድረስ በኢትዮጵያ ምድር የተፈራረቁት ነገስታትና መሪዎች አንዳቸውም ‘ተጠያቂው እኔ ነኝ!’ ብለው በገሀድ በማወጅ የድርጊታቸውን ውጤት አሜን ብለው የተቀበሉበት አጋጣሚ የለም፡፡ ሌላው ደግሞ የፍርድ አሰጣጡ (በተለይ የሁለተኛው ፍርድ) በራሱ ትልቅ መልዕክት ያስተላልፋል፡፡ በልዩነት ሀሳብ ጥፋቱ የንጉሱ እንደሆነ ያለፍርሃት የተናገሩት ፈራጅ ንጉሱን ተጠያቂ ለማድረግ በውስጣቸው የተፈጠረው ነጻነትና ድፍረት ድንገታዊ ነው ለማለት ይከብዳል፡፡ አጼ ቴዎድሮስ አስተዳደራዊ ብልሹነት ለማስወገድና የመንግስት ተጠያቂነት የሰፈነበት መልካም አስተዳደር ለመትከል ያደረጉት ጥረትና የያዙት ጠንካራ አቋም በጊዜው የነበረውን የአገዛዝ ስርዓት መንፈስ ያንጸባርቃል፡፡ ይህንን ለመረዳት ከቴዎድሮስ ቀጥሎ የተነሱትን ገዢዎች በአደባባይ በጥፋተኝነት መፈረጅ የሚያስከትለውን መዘዝ ማሰብ ብቻ ይበቃል፡፡ የዳኝነት ነጻነት ባልሰፈነበት ስርዓት ውስጥ የአገር መሪ ላይ ጣት መቀሰር ጣት ያሳጣል፡፡ ባስ ሲልም ህይወት ያሳጣል፡፡
ንጉስ ሊከሰስ መቻሉ በኢትዮጵያ የአስተዳደር ህግ ታሪክ ውስጥ ብቻ ሳይሆን ድንበር ደፍረው ሊያጠቋቸው የመጡትን እንግሊዞች ሳይቀር ማስደመሙ አይቀርም፡፡ እርግጥ ነው በዚያን ዘመን እንግሊዝ በኅይል አሰላለፍ፣ በጦር መሳሪያ ብዛትና ጥራት ብሎም በኢኮኖሚ ዕድገት ከኢትዮጵያ መጥቃ ሄዳለች፡፡ ሆኖም እ.ኤ.አ እስከ 1947 ዓ.ም. ድረስ በእንግሊዝ ምድር ‘ንጉስ አይከሰስም፣ ሰማይ አይታረስም’ ነበር፡፡ በዚሁ ዓመተ ምህረት የወጣው Crown Proceedings Act 1947 ያለመከሰስ መብትን እስኪያስወግድ ድረስ በእንግሊዝ አገር መንገስት ከውል ውጭ ኃላፊነት ላደረሰው ጉዳት ዜጋው በቀጥታ ክስ አቅርቦ ዳኝነት ማግኘት አይችልም፡፡ አንድ የአገሬው ምሁር በጊዜው የነበረውን ሁኔታ እና ያለመከሰስ መብት በህግ ቀሪ መደረጉን እንደሚከተለው ይገልጸዋል፡፡
There is one public authority that was immune from torts at common law: the Crown. ‘The King can do no wrong’ is an old slogan of the common law. And a tort is a wrong. So at common law the Crown was not liable in tort. … ‘the King can do no wrong’ can mean either ‘it is not unlawful if the King did it’, or ‘if it was unlawful, it was not the King who did it’… But the Crown Proceedings Act 1947 abolished the immunity. For most purposes, the Crown is liable in tort and breach of contract in the same way as a private individual.[8]
የጊዜው ርዝመት ስንለካው አጼ ቴዎድሮስ ንጉስ የሚከሰስበትን ስርዓት በይፋ በመቀበል እንግሊዞችን በአንድ ክፍለ ዘመን ቀድመዋል፡፡
[1] በበርካታ የህግ ትምህርት ቤቶች የአስተዳደር ህግ ትኩረት ያላገኘና መምህሩ በ assignment የሚገላገለው ኮርስ ሆኖ ቀርቷል፡፡ በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶችም በቁጥር በጣም ውስን ናቸው፡፡
[2] የአስተዳደር ህግ የአንዲት አገር ፖለቲካዊ፣ ዲሞክራሲያዊና ህገ መንግስታዊ ስርዓት ነፀብራቅ ነው፡፡ የላይኛው ካላማረ የታችኛውም አያምርም፡፡
[3] አሁንም ድረስ ኢትዮጵያ ውስጥ ፖለቲካና አስተዳደር መሀላቸው ንፋስ አይገባም፡፡ ፖለቲከኛ አስተዳዳሪ ነው፡፡ አስተዳዳሪም ፖለቲከኛ ነው፡፡ ሙያተኝነት (professionalism) በታማኝነት ተውጧል፡፡
[4] ፓርላማና ፍርድ ቤቶች ስራ አስፈጻሚውን ከመቆጣጠር ይልቅ በተገላቢጦሹ ይቆጣጣራቸዋል፡፡ በስልጣን ቁጥጥር ረገድ ሚናቸው አንድም ‘ምንም’ ወይም አሊያም ‘ከምንም የሚሻል’ ዓይነት ዝቅተኛ ነው፡፡
[5] መዝገቡ ምትኬ “በሥልጣን ያላግባብ መገልገል ወንጀልና ሕግ: በኢትዮጵያ አንዳንድ ሐሳቦች” ሕግና ፍትሕ፡ በኅብረተሰባዊት ኢትዮጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግስት ልዩ ፍርድ ቤት ቅ.3 ቁ 1. መጋቢት 1978 ዓ.ም. ገፅ 26-55
[6] ጳውሎስ ኞኞ, አጤ ቴዎድሮስ (አዲስ አበባ 1985 ዓ.ም.) ገፅ 146
[7] አበራ ጀምበሬ፤ የኢትዮጵያ ሕግና የፍትሕ አፈጻጸም ታሪክ፡ ከ1426 እስከ 1996 ዓ.ም. (ሻማ ቡክስ 2006 ዓ.ም.) ገፅ 149-150
[8] Timothy Endicott, Administrative Law (2nd. edn, Oxford University Press, 2011) ገፅ 531
Filed under: Articles, Ethiopian Constitutions
