የመቃወም አቤቱታ —የሰበር ችሎት የህግ ትርጉም
1. ፍርድ መቃወም
ተካፋይ ባልሆነበት ክርክር የተሰጠው ውሳኔ መብቴን ይነካል በማለት አስቀድሞ ለአንድ ወገን የተሰጠውን ውሳኔ ለማሰረዝ በመቃወም አመልካች የሚቀርብ አቤቱታ
የመቃወም አቤቱታ ሲቀርብ ክርክሩ የሚካሄደው በመቃወም አመልካች እና አስቀድሞ በተሰጠው ውሳኔ ተጠቃሚ በሆነው የመቃወም ተጠሪ በሚባለው ወገን መካከል ሲሆን የዚህ ዓይነቱ ክርክር የሚቀርብበት እና የሚመራበት ስርዓት እንዲሁም የዚህ ዓይነቱን ክርክር የሚሰማው ፍርድ ቤት ስላለው ስልጣን በፍትሐብሔር ስነ ስርዓት ሕግ ከቁጥር 358 እስከ 360 ተመልክቷል፡፡
የመቃወም አቤቱታው መቅረብ የሚገባው በፍትሐብሔር ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 222 እና 223 ድንጋጌዎች መሰረት ክስ እና የማስረጃ መግለጫ የሚቀርብበትን ስርዓት መሰረት በማድረግ ስለመሆኑ በግልጽ ተደንግጎአል፡፡
የመቃወም አቤቱታው እና የማስረጃው ቅጂ የመቃወም ተጠሪ ለሆነው ወገን እንዲደርስ መደረግ የሚገባው መሆኑን ከመግለጽ በስተቀር የመቃወም ተጠሪው የጽሁፍ መልስ እና የመከላከያ ማስረጃ ማቅረብ እንደሚገባው በእነዚህ ድንጋጌዎች ላይ በግልጽ የተጻፈ ባይሆንም የመቃወም ተጠሪ የሆነው ወገን በፍትሐብሔር ስነ ስርዓት ሕግ ቁጥር 234 ድንጋጌ መሰረት ለቀረበበት የመቃወም አቤቱታ ያለውን የመከላከያ መልስ እና ማስረጃ ማቅረብ የሚገባው ስለመሆኑ ከቁጥር 360(1) እና (2) ድንጋጌዎች ጣምራ ንባብ መገንዘብ ይቻላል፡፡ በተለይም የመቃወሚያው ክርክር የሚሰማው የመጀመሪያው ክርክር በተሠማበት ስነ ስርዓት መሰረት ስለመሆኑ በቁጥር 360(2) የተመለከተው አስገዳጅ ድንጋጌ በቀጥታ የቀረበ ክስ እና ክርክር የሚስተናገድበትን ስርዓት በተመለከተ በፍትሐብሔር ስነ ስርዓት ሕጉ የተመለከቱት መሰረታዊ ድንጋጌዎች የመቃወሚያ ክርክርን በማስተናገድ ረገድም በተመሳሳይ ሁኔታ ተፈጻሚ ሊደረጉ የሚገባቸው መሆኑን በግልጽ የሚያስገነዝብ ነው፡፡
በዚህ ድንጋጌ የተመለከተው የክርክር አመራር ስርዓት ዓይነተኛ ዓላማ ሁለቱም ተከራካሪ ወገኖች እኩል ዕድል እንዲኖራቸው እና በተለይም የመቃወም አመልካች የሆነው ወገን የክርክሩ ተካፋይ ባልነበረበት ጊዜ የቀረበውን የመቃወም ተጠሪ ወገን የሰው እና የሰነድ ማስረጃ በመስቀልኛ ጥያቄ እና በማስተባበያ ክርክር ጭምር የመፈተን ዕድል እንዲያገኝ ለማስቻል እንደሆነ ይታመናል፡፡
ሰ/መ/ቁ. 86398 ቅጽ 16፣[1] ፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 222፣ 223፣ 350-360
የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 358 አንድ የክርክሩ ተካፋይ መሆን የሚገባው ሰው የክርክሩ ተካፋይ ሳይሆን ውሳኔ ተሰጥቶ ከሆነ እና ውሳኔውም ያረፈው በአንድ የክርክሩ ምክንያት በሆነ ንብረት ላይ ሁኖ ይህንኑ የክርክሩ ተካፋይ ያልሆነ ወገንን መብትና ጥቅም የሚነካ መሆኑ ከተረጋገጠ ፍርዱ ይኸው ወገን ባለበት እንዲታይና በሕግና በማስረጃ የተደገፈ ሁኖ ሲገኝ እንዲነሳለት የሚደነግግ ነው፡፡ አቤቱታው የሚቀርብበት ሥርዓትም በቁጥር 359 ስር በተመለከተው መንገድ መሆን እንደአለበት የተቀመጠ ሲሆን ይህ ድንጋጌ የመቃወሚያ አቤቱታ አቀራረብ በክስ አመሰራረት አይነት ሁኖ ማስረጃ ዝርዝር ሁሉ ይህንኑ ስርዓት ማሟላት እንደአለበት ያስገነዝባል፡፡ የዚህ ድንጋጌ ይዘቱና መንፈሱ ሲታይ ክርክሩ መኖሩን ከጅምሩ እያወቀ ውጤቱን በመጠበቅ ከፍርዱ በኋላ የፍርድ መቃወሚያ የሚያቀርበውን ወገን አቤቱታውን በመቀበል ለማስተናገድ አስፈላጊ ያለመሆኑን ሁሉ ያስገነዝባል፡፡
ይህም የክርክር አቀራረብ በቅን ልቦና የተመሰረተ ሁኖ በአነስተኛ ወጪ፣ ጉልበትና አጭር ጊዜ ፍትሐዊነት ያለውን ውሳኔ ለመስጠት የሚቻልበት አግባብ እንዲኖር እና ሕግ አውጪ ከፈለገበት አላማ ጋር መጣጣም ያለበት መሆኑም የሚታመን ነው፡፡ እንግዲህ አቤቱታውን የሚያቀርበው ወገን የቅን ልቦና ተከራካሪ ሁኖ መሰረታዊ መብቱን ማስከበር የሚችልበት የስነ ስርዓት ሕግ አግባብ እንዲኖር ሕግ አውጪ የፈለገ ሲሆን ይህንኑ መመዘኛ የሚያሟላ አቤቱታ አቅራቢ የሚቃወመው ፍርድ ዋጋ ያለው፣ ያልተፈፀመ መሆን እንደአለበትም የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 358 ድንጋጌ ይዘት ያስረዳል፡፡ በሌላ አገላለፅ የፍርድ መቃወሚያ የሚቀርብበት ፍርድ ስልጣን ባለው ፍርድ ቤት ያልተሻረና አፈጻጸሙም ያልተጠናቀቀ ሊሆን እንደሚገባ ሕጉ ያሳያል፡፡
ሰ/መ/ቁ. 93987 ቅጽ 17፣[2] ፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 358፣ 359
የሟች ሀብት ተጣርቶ በክፍፍሉ ላይ ውሳኔ ከተሰጠ በኋላ ውርሱ ሲጣራ ያልተሳተፈ የሟች ወራሽ ነኝ የሚል ወገን በፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 358 መሰረት መቃወሚያ ማቅረብ ያለበት በውርስ አጣሪው ሪፖርትና ሪፖርቱን ባፀደቀው ፍ/ቤት ሳይሆን የክፍፍሉን ጥያቄ አይቶ ውሳኔ ለሰጠው ፍርድ ቤት ነው፡፡
የውርስ አጣሪ ሪፖርት በፍርድ ቤት መጽደቅ በራሱ ፍርድ ሁኖ ለአፈፃፀም የሚቀርብ ሣይሆን እንደማስረጃ የሚያገለግል ነው፡፡ በመሆኑም ሪፖርቱ የማስረጃነት ዋጋ አለው ከተባለ ደግሞ የክፍፍል ክርክር ሲቀርብ በማስረጃነቱ ላይ ክርክር ቢቀርብ ክርክሩ መቅረብ ያለበት በውርስ አጣሪና ሪፖርቱን በአፀደቀው ፍርድ ቤት ነው ተብሎ ውድቅ የሚሆንበት ሕጋዊ ምክንያት የለም፡፡
ሰ/መ/ቁ. 45905 ቅጽ 11፣[3] ፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 358፣ ፍ/ህ/ቁ. 944፣ 946፣ 956፣ 960
ተከራካሪ ወገኖች በፍርድ ቤት የሚያካሂዱትን ሙግት በማቋረጥ የሚያደርጉት የእርቅ ስምምነት በፍርድ ቤት ትእዛዝ ተረጋግጦና ለሚመለከተው ክፍል ይተላለፍ መባሉ የፍርድ ያህል አስገጃጅነት ያለው በመሆኑ እርቁን ያፀደቀው ፍርድ ቤት እርቁ ለሕግና ለሞራል ተቃራኒ አይደለም በእርቁ መሠረት ይፈፀም በማለት በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ መንገድ የሰጠውን ትእዛዝ በፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 358 መሰረት በእርቅ ስምምነቱ መብቴ ተነክቷል በሚል ወገን ተቃውሞ ሊቀርብበት የሚችል ነው፡፡
ሰ/መ/ቁ. 83582 ቅጽ 15[4]
2. ንብረት እንዳይያዝ
በአፈጻጸም ንብረት እንዳይያዝ፣ እንዳይታገድ በንብረቶቹ ላይ መብት አለኝ የሚል በክርክሩ ተሳታፊ ያልሆነ ሶስተኛ ወገን የሚያቀርበው አቤቱታ
የፍ/ብ/ህ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ. 418 ድንጋጌ አስፈላጊነት የክርክሩ አካል ያልሆኑና ፍርድ ያላረፈባቸው የ3ኛ ወገን ንብረት ሳይረጋገጥ ለፍርዱ ማስፈፀሚያነት እንዳይውሉ ለመከላከልና ባንጻሩ ፍርዱን የመፈፀም ለማስተጓጉል (እንዳይፈፀም ለሚቀርቡት በቂ ላልሆኑ አቤቱታዎችም) እልባት የሚሰጥ ነው፡፡ በመሆኑም በተያዙት ንብረቶች ላይ መብት አለኝ የሚል ወገን የሚያቀርበውን መቃወሚያና አቤቱታ ተቀብሎ መመርመር እንዳለበት የተጠቀሰው ድንጋጌም በግልፅ ያሰፈረው ነው፡፡ ይህ ከሆነ የዚሁ አንቀጽ 418(3) የአራተኛው ቅጂ ባለይዞታነትን ለማስረዳት የፅሁፍ ማስረጃ መቅረብ እንዳለበት የሚደነግግ ቢሆንም የእንግሊዘኛው ቅጂ የስነ- ስርዓት ህጉ ደግሞ ይህንኑ አንቀጽ ሲገልጽ The Claimant or 0bjector Shall adduce evidence to Show that and the date of the attachment he had Some interest in or was possessed of the property attached ይላል፡፡ እንግዲህ ከዚህኛው የእንግሊዘኛ ቅጂ የምንረዳው ማስረጃ በማቅረብ ለአፈጻጸም የቀረበውን ንብረት ማስረዳት እንደሚቻል የሚገልጽ ነው፡፡ የአማርኛው ቅጂም ቢሆን ከፍ/ህ/ቁ/1193 (1) እና (2) ድንጋጌዎች ጋር ተደምሮ ሲታይ ሌላውን የማስረጃ አይነት በግልጽ እንዳይቀርብ የከለከለው ሆኖ አይታይም፡፡
ሰ/መ/ቁ 97094 ቅጽ 17፣[5] ፍ/ህ/ቁ. 1193(1) (2)፣ ፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 418
በዋናው ክርክር የሚሰጠው ውሳኔ እና በውሳኔው መሠረት ለማስፈጸም የሚደረገው ሂደት የተለያዩ በመሆናቸው በሚቀርቡት መቃወሚያዎች ላይ የሚሰጡት ውሳኔዎችም የተለያዩ ናቸው፡፡ መቃወሚያ አቅራቢው መብቱ የተነካው በአፈጻጸም ሂደቱ ከሆነ ከአፈጻጸም ሂደቱ ጋር የተያያዘ መገፍትሄ ነው የሚሰጠው፡፡ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁ. 418 መሠረት በሚቀርብ መቃወሚያ ላይ የሚሰጠው ውሳኔ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁ. 419 ተመልክቶአል፡፡ በዚህ መሠረት መቃወሚያው ተቀባይነት ያገኘ ከሆነ በአፈጻጸም የተያዘው ንብረት በከፊል ወይም በሙለ እንዲለቀቅ ትዕዛዝ ይሰጣል፡፡ ከዚህ አልፍ በአፈጻጸም የተያዘው ንብረት ለአንድ ወይም ለሌላው ተከራካሪ ወገን ይገባል የሚል ዳኝነት አይሰጥም፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ በዋናው ክርክር የተሰጠውን ውሳኔ የሚሽር ወይም የሚያሻሽል ውሳኔ አይሰጥም፡፡ የዚህ አይነት ውሳኔ መስጠት የሚቻለው ዋናውን ውሳኔ በመቃወም አቤቱታ ሲቀርብ ነው፡፡ ይህ ደግሞ እራሱን የቻለ የአቀራረብ ሥርዓት እና የክርክር አመራር ሂደት ያለው ነው፡፡ በዚህ ረገድ ተገቢው ድንጋጌም በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕግ ቁ. 358 የተመለከተው ነው፡፡
ሰ/መ/ቁ. 53607 ቅጽ 12[6]፣ ፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 358፣ 418፣ 419
በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 418 አግባብ የተሟላ ክርክርና ማስረጃ ያቀረበ ወገን አቤቱታው በመደበኛ ሙግት እንዲከናወን እንዳይጠይቅ ሕጉ ግልጽ ክልከላ ያላደረገበት ሲሆን በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁጥር 421 ስር የተጠበቀው መብትም በሕጉ አግባብ የሚቀርቡ መቃወሚያዎች እንደተጠበቁ ሁነው አመልካቹ በምርጫው እንዲጠቀምበት የተቀመጠ እንጂ ይህንኑ ስርዓት እንዲከተል የግድ የሚደረግበት ያለመሆኑ ድንጋጌው በፈቃደኝነት የአቀራረፅ ስርዓት መቀመጡ አስረጂ ነው፡፡
ሰ/መ/ቁ 86133 ቅጽ 15[7]
የቀዳሚነት መብት አለኝ በሚል መቃወሚያ አቅርቦ ጥያቄው ውድቅ የተደረገበት ሰው በድጋሚ ክስ ማቅረብ የተፈቀደለት በአፈፃፀም ችሎት የንብረቱ ባለመብትነት በጭብጥነት ተይዞ በመደበኛው የሙግት ስርአት አይነት ከግራ ቀኙ ክርክርና ማስረጃ አንፃር ተመርምሮ ውሳኔ የሚሰጥበት ባለመሆኑ ይህንን እድል ለመስጠት ነው፡፡ አመልካቹ ይህንን መብት የሚያስከብርለት ሌላ ክስ የመሰረተ ከሆነ ግን የፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 421 ክስ ለማቅረብ ስለሚፈቅድ ብቻ በተመሳሳይ ጉዳይ ዳግመኛ ክስ ማቅረብ የስነ-ስርአት ህጉ አላማ አይደለም፡፡
ሰ/መ/ቁ. 37214 ቅጽ 9፣[8] ፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ. 421
[1] አመልካች ወ/ሮ አሰለፈች ይመር እና ተጠሪዎች እነ ወ/ሮ አስመረት ተወልደ /3 ሰዎች/ ሐምሌ 28 ቀን 2006 ዓ.ም.
[2] አመልካች እነ አቶ ዳንኤል ወንዳፈራ /2 ሰዎች/ እና ተጠሪ እነ ወ/ሮ አስናቀች ቦጋለ /4 ሰዎች/ ሐምሌ 18 ቀን 2006 ዓ.ም.
[3] አመልካች ሚስስ ሚላን ፑሲጂ /2 ሰዎች/ እና ተጠሪ እነ ሐንድሬ ፒስ ማልጂ /2 ሰዎች/ ጥቅምት 3 ቀን 2003 ዓ.ም.
[4] አመልካች ወ/ሮ ወርቅነሽ ውብነህ ተጠሪዎች እነ ወ/ሮ አልማዝ ዓለሙ /3 ሰዎች አንደኛው በሌሉበት/ መጋቢት 27 ቀን 2005 ዓ.ም.
[5] አመልካች ወ/ሮ አስቴር አምባው እና ተጠሪዎች እነ አቶ አበባው ክፍሌ /2 ሰዎች/ ህዳር 8 ቀን 2ዐዐ7 ዓ.ም.
[6] አመልካች የምጥን መንደር መኖሪያ ቤቶች የህብረት ሥራ ማህበር እና ተጠሪዎች እነ ወ/ሮ ባየች አይገምት /3 ሰዎች 2 ሰዎች በሌሉበት/ ህዳር 14 ቀን 2003 ዓ.ም.
[7] አመልካች እነ አቶ ፍቅሩ ከበደ /11 ሰዎች/ እና ተጠሪ ወ/ሮ አስቴር አርአያ /2 ሰዎች/ ጥቅምት 20 ቀን 2006 ዓ.ም.
[8] አመልካች አቶ ተስፊዬ አለሙ እና ተጠሪ እነ ሐጂ ይማም ሙዘይን /3 ሰዎች/ የካቲት 25 ቀን 2002 ዓ.ም.
Filed under: Articles, Case Comment
