Quantcast
Channel: Ethiopian Legal Brief
Viewing all articles
Browse latest Browse all 992

የመጨረሻ ውሳኔ፡ የሰበር ችሎት ውሳኔዎች ዳሰሳ

$
0
0

የመጨረሻ ውሳኔ፡ የሰበር ችሎት ውሳኔዎች ዳሰሳ

በአዋጅ ቁ. 25/88 አንቀጽ 10 በሰበር ችሎት ስልጣን ስር የሚወድቁ ጉዳዮች በስር ፍርድ ቤት በይግባኝ ወይም በመደበኛ ስልጣን የመጨረሻ ውሳኔ የተሰጠባቸው መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ የመጨረሻ ውሳኔ ሲባል ምን ማለት እንደሆነ በአዋጁ ትርጓሜ አልተሰጠውም፡፡ በአንቀጽ 10(2) የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት መደበኛ ችሎት ግራ ቀኙን አከራክሮ ውሳኔ ሲሰጥ ውሳኔ መሰጠቱ በራሱ የመጨረሻ የሚያደርገው በመሆኑ የመጨረሻ ፍርድ ትርጉም ከዚህኛው ድንጋጌ አንጻር አደናጋሪ አይሆንም፡፡ የይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ውሳኔም የስር ፍርድ ቤትን ውሳኔ ሙሉ በሙሉ በመሻር ወይም በማጽናት ከተሰጠ የይግባኝ አቅራቢውን ተከራካሪ ወገን ማንነት መሰረት በማድረግ ውሳኔው የመጨረሻ ስለመሆኑ መለየት አይከብድም፡፡ መሰረታዊው ቁምነገር አንድ ተከራካሪ ወገን ከአንድ ጊዜ በላይ ይግባኝ የማቅረብ መብት የሌለው መሆኑ ነው፡

ይሁን እንጂ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የስር ፍርድ ቤትን ውሳኔ በከፊል በማሻሻል ውሳኔ ሲሰጥ ውሳኔው በከፊል የመጨረሻ ፍርድ ያገኘ፤ በከፊል ደግሞ ያላገኘ ስለሚሆን በአንቀጽ 10(1) እና (2) መሰረት የሰበር ችሎቱን ስልጣን ለመወሰን አስቸጋሪ ያደርገዋል፡፡ ይኼው ነጥብ በሰ/መ/ቁ 61480 (አመልካች ገ/እግዚአብሔር ከበደው እና ተጠሪ ወ/ት ሠላማዊት ወ/ገብርዔል ጥቅምት 22 ቀን 2004 ዓ.ም. ቅጽ 13) የተነሳ ሲሆን የስር ፍርድ ቤት ውሳኔ ተሻሽሎ በከፊል መለወጡ የመጨረሻ እንደሚያደርገው የህግ ትርጉም ተሰጥቶበታል፡፡ ሆኖም በዚህ መልኩ የህግ ትርጉም መስጠት ሊያስከትል የሚችለው የጎንዮሽ ችግር እንዴት እንደሚፈታ ችሎቱ በመፍትሔነት ያሰቀመጠው ነገር የለም፡


በመዝገቡ ላይ አመልካች በትግራይ ክልል የወረዳ ፍ/ቤት ተከሳሽ የነበሩ ሲሆን ተጠሪ ደግሞ ከሳሽ ናቸው፡፡ የወረዳው ፍርድ ቤት ተጠሪ (የስር ከሳሽ) የጠየቁትን ዳኝነት በሙሉ በመቀበል ብር 213450 (ሁለት መቶ አስራ ሶስት ሺ አራት መቶ ሃምሳ ብር) እንዲከፈላቸው ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ አመልካች (የስር ተከሳሽ) በውሳኔው ቅር በመሰኘት ለመቐሌ ዞን ከፍተኛው ፍርድ ቤት የይግባኝ አቤቱታ አቅርበው ፍርድ ቤቱም አመልካች ለክሱ ኃላፊ ናቸው የተባለበትን የስር ፍርድ ቤት የውሳኔ ክፍል ሳይቀይር ለተጠሪ እንዲከፈል የተባለውን የገንዘብ መጠን ግን በግማሽ ቀንሶ 123450 ብር (አንድ መቶ ሃያ ሶስት ሺ አራት መቶ ሃምሳ ብር) አመልካች እንዲከፍሉ ውሳኔ ሰጥቷል፡

አመልካች በዚህኛውም ውሳኔ ባለመስማማት የስር ፍርድ ቤቶች ውሳኔዎች መሰረታዊ የህግ ስህተት እንደተፈጸመባቸው በመግለጽ የሰበር አቤቱታ ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አቅርበዋል፡፡ የክልሉ ሰበር ችሎት የስር ፍርድ ቤቶች በጉዳዩ ላይ የተለያየ ውሳኔ እንደሰጡ በመጠቆም የመጨረሻ ውሳኔ ሳይኖር አመልካች የሰበር አቤቱታ ሊያቀርቡ አይችሉም በማለት አቤቱታውን ባለመቀበል መዝገቡን ዘግቶታል፡ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የመጨረሻ የሚባል ፍርድ ስለመኖሩ ጉዳዩን ከክልሉ ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ አንጻር የፈተሸው ሲሆን የወረዳውና ከፍተኛው ፍርድ ቤት የአመልካችን ኃላፊነት አስመልክቶ ተመሳሳይ ውሳኔ የሰጡ በመሆኑ ጉዳዩ የመጨረሻ ውሳኔ የተሰጠው ነው ሊባል እንደሚገባ ድምዳሜ ላይ ደርሷል፡፡ ምንም እንኳን መዝገቡ የታየው ከክልሉ ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ አንጻር ቢሆንም አዋጁ ከአዋጅ ቁ. 25/88 አንቀጽ 10 ጋር ተመሳሳይነት ባለው መልኩ የክልሉን ሰበር ሰሚ ችሎት የሰበር ስልጣን የሚወስን በመሆኑ በችሎቱ የተሰጠው የህግ ትርጉም ለችሎቱ ለራሱ ሳይቀር ፋይዳ አለው፡

ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው በችሎቱ የተሰጠው የህግ ትርጉም የጎንዮሽ ችግሮችን ለመፍታት አያስችልም፡፡ የከፍተኛው ፍርድ ቤት በማሻሻል የሰጠው ውሳኔ የመጨረሻ የሚሆነው ለአመልካች እንጂ ለተጠሪ አይደለም፡፡ ውሳኔው ተጠሪ በስር ፍርድ ቤት የተወሰነላቸውን የገንዘብ መጠን በግማሽ ቀንሶታል፡፡ ተጠሪ በውሳኔው ቅር ተሰኝተው ይግባኝ ሊያቀርቡ የሚችሉት ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት እንጂ ለሰበር ችሎቱ አይደለም፡፡ ይህ መሆኑ ደግሞ አንድና ተመሳሳይ ጉዳይ በአንድ ጊዜ በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤትና በክልሉ ሰበር ችሎት እንዲታይ ያደርገዋል፡፡ በዚህን ጊዜ የሰበር ችሎቱ መዝገቦቹን ማጣመር አለበት? ወይስ ተጠሪ ማቅረብ የሚችሉት መስቀለኛ የሰበር አቤቱታ ነው? በዚህ መልኩ አቤቱታ ማቅረብ መቻላቸው በራሱ የህግ ምላሽ የሚፈልግ ጥያቄ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ተጠሪ የይግባኝ አቤቱታ እንጂ መስቀለኛ የሰበር አቤቱታ ማቅረብ ፍላጎቱ ከሌላቸውስ? የተጠሪ የይግባኝ መብት የሚፈጸመው እንዴት ነው? በሰ/መ/ቁ 61480 እነዚህና መሰል ጥያቄዎች በጥልቀት ተመርምረው እልባት አላገኙም፡፡ ከዚህ አንጻር የችሎቱ ውሳኔ ራሱ የመጨረሻ ፍርድን አስመልከቶ የመጨረሻ እልባት የሰጠ ውሳኔ ነው ለማለት አይቻልም፡

ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት የስር ፍርድ ቤትን ውሳኔ ሙሉ በሙሉ በማጽናት ወይም በመሻር ውሳኔ ቢሰጥም ይግባኝ አቅራቢውን ተከራካሪ ወገን በተመለከተ የመጨረሻ ፍርድ የማይሆንባቸው አጋጣሚዎች ይኖራሉ፡፡ ይህም የሚሆነው የይግባኝ አቤቱታው ከመነሻው ይግባኝ የማይባልበት ጉዳይ ከሆነ ነው፡፡ ለምሳሌ በወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ 184 የትዕዛዝ ይግባኝ ስላለመኖሩ ተደንግጓል፡፡ በድንጋጌው ስር በተዘረዘሩት ጉዳዮች ላይ የይግባኝ አቤቱታ ቀርቦ አቤቱታው ቢሰረዝ ወይም ቢጸና የይግባኝ ሰሚውን ውሳኔ እንደ መጨረሻ ፍርድ በመቁጠር የሰበር አቤቱታ ሊቀርብ አይችልም፡፡

በወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ 184 ከተካተቱት ውስጥ ተከሳሽ በወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ 141(1) መሰረት እንዲከላከል የሚሰጥ ትዕዛዝ የማይገኝ ሲሆን በሌሎች ድንጋጌዎች ላይም በትዕዛዙ ላይ ይግባኝ ማቅረብ ስለመቻሉ/ስላለመቻሉ በግልጽ የተቀመጠ ነገር የለም፡፡ ሆኖም የሰበር ችሎት ከወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ 184 እና 185 ጣምራ ንባብ በመነሳት ተከሳሽ እንዲከላከል በተሰጠው ትዕዛዝ ላይ ይግባኝ ማቅረብ እንደማይችል መጀመሪያውኑ ይግባኝ ማቅረብ በማይችልበት ጉዳይ ይግባኝ አቅርቦ ይግባኙ ቢሰረዝ የይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ትዕዛዝ/ውሳኔ የመጨረሻ ፍርድ ሊባል እንደማይገባ በሰ/መ/ቁ 74041 (አመልካች እነ አንተነህ መኮንን እና ተጠሪ የፌደራል ስነ-ነግባርና ጸረ-ሙስና ኮሚሽን ዓቃቤ ህግ ሰኔ 4 ቀን 2004 ዓ.ም. ቅጽ 13) የህግ ትርጉም ሰጥቷል፡፡

በተመሳሳይ መልኩ በወንጀል ጉዳይ ተከሳሽ በሌለበት ፍርድ ሲሰጥ ክርክሩ እርሱ ባለበት እንዲታይ አቤቱታ አቅርቦ ውድቅ ካላስደረገውና አቤቱታው ተቀባይነት ካጣ በሌለበት ታይቶ የተሰጠው ፍርድ እንደመጨረሻ ፍርድ ተቆጥሮ በሰበር ሊታረም አይችልም፡፡ (አመልካች ሰማኸኝ በለው እና ተጠሪ የፌደራል ዐቃቤ ህግ ታህሳስ 25 ቀን 2003 ዓ.ም. ሰ/መ/ቁ 57632 ቅጽ 12 በተጨማሪም ሰ/መ/ቁ 59537 ቅጽ 12 እና 74041 ቅጽ 13 ይመለከቷል፡፡)

ከክልል የሚነሱ ጉዳዮች በሰበር ሊታዩ የሚችሉት የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመደበኛ ችሎት ወይም በይግባኝ አይቶ የመጨረሻ ውሳኔ የሰጠባቸው ጉዳዮች ሲሆኑ ነው፡፡ (አዋጅ ቁ 25/88 አንቀጽ 10(3) የጉዳዩ ዓይነት የክልል ወይም በተመሳሳይ ጊዜ የክልልና የፌደራል በሚሆንበት ጊዜ በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በይግባኝ የሚሰጥ ውሳኔ የመጨረሻ ውሳኔ አይደለም፡፡ የመጨረሻ የሚሆነው በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ከታየ በኋላ ነው፡፡ (አመልካች ኢትዮ ቴሌኮም ደቡብ ምዕራብ እና ጋምቤላ ሪጅን እና ተጠሪ ወ/ሮ ሳባ መንገሻ ሚያዝያ 21 ቀን 2006 ዓ.ም. ሰ/መ/ቁ 94102 ቅጽ 16 እንዲሁም (አመልካች መተሃራ ስኳር ፋብሪካ እና ተጠሪ እነ ጥበቡ እሸቱ (139 ሰዎች) መጋቢት 22 ቀን 2006 ዓ.ም. ሰ/መ/ቁ 94869 ቅጽ 16 ይመለከቷል፡፡) በሁለቱም መዝገቦች በክልል የታዩ የስራ ክርክሮች እንደ መጨረሻ ፍርድ ተቆጥረው በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሚታዩበት አግባብ በጭብጥነት ተይዞ እልባት አግኝቷል፡፡ በዚሁ መሰረት ከክልል መነሻ ያደረገ የስራ ክርክር በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት (ችሎቱ በክልሉ ከተደራጀ) ከመቅረቡ በፊት በቀጥታ ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ለመቅረብ ብቁ አይደለም፡

በሰ/መ/ቁ 94102 ክሱ መጀመሪያ የታየው በጅማ ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት ሲሆን ፍርድ ቤቱ በሰጠው ውሳኔ ላይ ተከሳሽ የነበረው አመልካች ለጅማ ዞን ከፍተኛው ፍርድ ቤት የይግባኝ አቤቱታ ያቀረበ ሲሆን አቤቱታው ተቀባይነት ሳያገኝ የስር ፍርድ ቤት ውሳኔ ጸንቷል፡፡ በመቀጠል አመልካች በቀጥታ ለፌደራሉ ሰበር ሰሚ ችሎት የሰበር አቤቱታ አቅርቧል፡፡ ሆኖም ችሎቱ ጉዳዩ ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ቀርቦ የመጨረሻ ውሳኔ ሳይሰጠው በቀጥታ ለፌደራል ሰበር ሰሚ ችሎት ለመቅረብ ብቁ እንዳልሆነ ገልጾ ውድቅ አድርጎታል፡፡

በሰ/መ/ቁ 94869 ጉዳዩ የተጀመረው በምስራቅ ኦሮሚያ አሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ወሳኝ ቦርድ ሲሆን ቦርዱ ተጠሪዎችና ሌሎች ሠራተኞች ያቀረቡትን ክስ የከፊሎቹን ይርጋን መሰረት በማድረግ የቀሩትን ደግሞ ስልጣን የለኝም በማለት ውድቅ አድርጎታል፡፡ ተጠሪዎች በውሳኔው ቅር በመሰኘት ለክልሉ ጠቅለይ ፍርድ ቤት የይግባኝ አቤቱታ ያቀረቡ ሲሆን ፍርድ ቤቱም ቦርዱ የሰጠውን ብይን በመሻር በፍሬ ነገሩ ላይ ውሳኔ እንዲሰጥ መዝገቡን ለቦርዱ መልሶታል፡፡ አመልካች የሰበር አቤቱታ ያቀረበውም የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሰጠው ውሳኔ ላይ ነው፡፡ ሆኖም አመልካች ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሰበር አቤቱታ ሳያቀርብ ለፌደራሉ ሰበር ችሎት በቀጥታ የሰበር አቤቱታ ማቅረብ እንደማይችል ተገልጾ አቤቱታው ውድቅ ተደርጎበታል፡፡

በሁለቱም መዝገቦች ላይ የስራ ክርክር ከሌሎች ክርክሮች በተለየ የተከራካሪውን ወገን ማንነት ከግምት ውስጥ በማስገባት የክልልና የፌደራል ተብሎ ሊከፈል እንደማይገባና የክልል ፍርድ ቤቶች የስራ ክርክርን የሚያዩት በውክልና ስልጣናቸው እንዳልሆነ አቋም ተይዞበታል፡፡ ከዚህ አንጻር በሰ/መ/ቁ 94102 አመልካች የጅማ ዞን ከፍተኛው ፍርድ ቤት በሰጠው ውሳኔ ላይ ለክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት የሰበር አቤቱታ ሳያቀርብ በቀጥታ ለፌደራሉ ሰበር ችሎት የሰበር አቤቱታ ሊያቀርብ አይችልም፡፡

ተመሳሳይ የችሎቱ አቋም በሰ/መ/ቁ 94869 ላይም ተንጸባርቋል፡፡ ሆኖም የጉዳዩ መነሻ የክልሉ አሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ወሳኝ ቦርድ በመሆኑ የችሎቱ ውሳኔ ግልጽ ስህተት የተሰራበት እንጂ ህጉ በአግባቡ የተተረጎመበት አይደለም፡፡ በአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ ቁ 377/96 አንቀጽ 140(1) እና 154(1) ግልጽ ሆኖ እንደተደነገገው ከማናቸውም ቋሚ ወይም ጊዜያዊ ቦርድ የተሰጠ ውሳኔ ይግባኝ የሚቀርበው ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ነው፡፡ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የምስራቅ ኦሮሚያ አሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ወሳኝ ቦርድ የሰጠውን ውሳኔ በይግባኝ ያየውም በውክልና ስልጣኑ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ስለሆነም ይህ ጉዳይ በክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በማናቸውም መልኩ ቢሆን ሊታይ አይችልም፡፡ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በይግባኝ አይቶ የመጨረሻ ውሳኔ የሰጠባቸው ጉዳዮችን የማየት ስልጣን የተሰጠው የፌደራሉ ሰበር ሰሚ ችሎት እንጂ የክልል ሰበር ሰሚ ችሎት እንዳልሆነ በአዋጅ ቁ 25/88 አንቀጽ 10(1) ተደንግጎ ይገኛል፡፡ ህጉ አሻሚነት የለውም፤ ግልጽ ነው፡፡ የችሎቱም ስህተት እንዲሁ ግልጽ ሆኖ ይታያል፡፡

በሰ/መ/ቁ 94102 እና 94869 ውሳኔ የተሰጠው በ2006 ዓ.ም. ሲሆን ከአምስት ዓመት በፊት በ2001 ዓ.ም. በሰ/መ/ቁ 37940 (አመልካች የኢትዮጵያ ወንጌላዊት ቤተክርስቲያን እና ተጠሪ ተስፋዬ ፀጋዬ ጥር 28 ቀን 2001 ዓ.ም. ያልታተመ) ችሎቱ ያንጸባረቀው ከአቋም ከሁለቱ መዝገቦች ተቃራኒ ነው፡፡ በዚህ መዝገብ ላይ የጉዳዩ መነሻ ተጠሪ የስር ከሳሽ በመሆን በአርባ ምንጭ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ያቀረቡት ክስ ሲሆን ፍ/ቤቱ ክሳቸውን ውድቅ በማድረጉ ይግባኝ ለጋሞ አካባቢ ከፍተኛ ፍ/ቤት የይግባኝ አቤቱታ አቅርበው ይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት የስር ፍ/ቤትን ውሳኔ ሽሮታል፡፡ አመልካቹ የሰበር አቤቱታ ያቀረበው የይግባኝ ሰሚው ፍ/ቤት ውሳኔ መሰረታዊ የህግ ስህተት ተፈጽሞበታል በሚል ነው፡፡ ችሎቱም ለክልሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በቅድሚያ የሰበር አቤቱታ አልቀረበም በሚል የአመልካችን አቤቱታ ውድቅ አላደረገውም፡፡

ሶስት ዳኞች የተሰየሙበት የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር አጣሪ ችሎት በዋናው ሰበር ሰሚ ችሎት መጣራት ያለባቸውን ነጥቦች ለይቶ በሚሰጠው ትዕዛዝ የመጨረሻ ሊባል አይችልም፡፡ (አመልካች አቶ ኃይሉ ዴሬሳ እና ተጠሪ ወ/ሮ ሱፌ አለሙየካቲት 6 ቀን 2006 ዓ.ም. ሰ/መ/ቁ 90928 ቅጽ 15) በዚህ መዝገብ ላይ ከስር ፍርድ ቤት ጀምሮ ለክርክሩ መነሻ የነበሩት መኖሪያ ቤትና ሰርቪስ ቤት የጋራ ንብረት ናቸው በማለት ጉዳዩን በይግባኝ ባየው የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔ በመሰጠቱ አመልካች በውሳኔው ቅር በመሰኘት ለክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሰበር አቤቱታ አቅርበዋል፡፡ የሰበር አጣሪ ችሎቱ አቤቱታውን መርምሮ ሰርቪስ ቤቶቹ የጋራ ናቸው የመባሉን አግባብነት ለማጣራት በሚል አቤቱታው ለሰበር ችሎቱ እንዲቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ አቤቱታው በክልሉ ሰበር ሰሚ ችሎት እየታየ እያለ አመልካች በዋናው መኖሪያ ቤት ላይ ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሰበር አቤቱታ አቅርበዋል፡፡ አቤቱታውን ሊያቀርቡ የቻሉትም አጣሪ ችሎቱ ሰርቪስ ቤቶቹን ብቻ በተመለከተ ያስቀርባል ማለቱ በዋናው ቤት ላይ ለክልሉ ሰበር ችሎት የቀረበው አቤቱታ ተቀባይነት እንዳጣ ያስቆጥረዋል በማለት ነው፡፡

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የአመልካችን አቤቱታ ከመረመረ በኋላ አቤቱታው የመጨረሻ ፍርድ ባገኘ ጉዳይ ላይ የቀረበ ባለመሆኑ ለሰበር ለመቅረብ ብቁ አይደለም በማለት ውድቅ አድርጎታል፡፡ ለዚህም የተሰጠው ምክንያት በአጣሪ ችሎቱ የተሰጠው ትዕዛዝ ጊዜያዊ አገልግሎት ያለው ከመሆኑም በላይ አምስት ዳኞች የሚሰየሙበት የክልሉ ሰበር ችሎት በአጣሪ ችሎት በተያዘው ጭብጥ ላይ ሳይገደብ በሌሎች ነጥቦችም ላይ ጭብጥ በመመስረት ተገቢውን ውሳኜ መስጠት የሚችል በመሆኑ ነው፡፡


Filed under: Articles, Case Comment

Viewing all articles
Browse latest Browse all 992

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>