ማውጫ
ከአምስት ያላነሱ ዳኞች
ምንም ምክንያት የሌለው ውሳኔ
በቅጽ ውስጥ ያልተካተቱ (ያልታተሙ) ውሳኔዎች
ወደኋላ ተመልሶ ስለመስራት (retro-activity)
የህግ ትርጉም መለወጥ
ሰበር ውሳኔ የሰጠበት ህግ ‘ሲሻር’ የውሳኔው የአስገዳጅነት ውጤት
የሰበር ውሳኔ አስገዳጅነት ፡የሰበር ውሳኔዎች ዳሰሳ
ከአምስት ያላነሱ ዳኞች
የሰበር ችሎት የህግ ትርጉም በስር ፍርድ ቤቶች አስገዳጅነት የሚኖረው ከአምስት ያላነሱ ዳኞች በተሰየሙበት የተሰጠ እንደሆነ ነው፡፡ [አዋጅ ቁ 454/1997 የፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅን እንደገና ለማሻሻል የወጣ አዋጅ አንቀጽ 2(1) ] ለሰበር የሚቀርብ አቤቱታ በዋናው ችሎት ከመታየቱ በፊት ሶስት ዳኞች በተሰየሙበት አጣሪ ችሎት ያስቀርባል ተብሎ ትዕዛዝ መሰጠት አለበት፡፡ [አዋጅ ቁ 25/88 አንቀጽ 22(1)] አቤቱታው አያስቀርብም ከተባለ ውድቅ ተደርጎ መዝገቡ ይዘጋል፡፡ አያስቀርብም የሚል ትዕዛዝ የስር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ ለሰበር የሚያበቃ መሰረታዊ ስህተት እንደሌለበት ከሚያመለክት በስተቀር እንደ ህግ ትርጉም አይቆጠርም፡፡ ይህም የአጣሪ ዳኞች ቁጥር ከአምስት ማነሱ ጋር ተዳምሮ ሲታይ ያስቀርባል/አያስቀርብም የሚል ትዕዛዝ በስር ፍርድ ቤቶች አስገዳጅነት እንደለሌለው ይጠቁመናል፡፡
በአመልካች የኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረቶች ጽ/ቤት እና ተጠሪ አቶ ጥበበ አየለ (ግንቦት 13 ቀን 2003 ዓ.ም. ሰ/መ/ቁ 59025 ቅጽ 12) መካከል በነበረው ክርክር በተመሳሳይ ጉዳይ ላይ አመልካች ያቀረበው የሰበር ቅሬታ ለሰበር ችሎቱ አያስቀርብም ተብሎ በመዘጋቱ የተያዘውም ጉዳይ በተመሳሳይ መንገድ መስተናገድ እንደሚገባው በተጠሪ በኩል ክርክር ቀርቧል፡፡ ችሎቱም በሶስት ዳኞች በአጣሪ ችሎት የሚሰጠው ትዕዛዝ አስገዳጅነት እንደሌለው በመጠቆም የተጠሪን ክርክር ውድቅ አድርጎታል፡፡
የሰበር አቤቱታ ያስቀርባል ከተባለ በኋላ ከሞላ ጎደል በሁሉም ጉዳዮች ክርክር የሚታየው በአምስት ዳኞች ነው፡፡ ሆኖም አንዳንድ ጊዜ በጣም መሰረታዊ የሆነ የህግ ትርጉም የሚያስነሳ ጉዳይ ሲኖር እንዲሁም ችሎቱ በፊት የነበረውን አቋም በግልጽ ሲቀይር ጉዳዩ የሚታየው በሰባት ዳኖች ነው፡፡ ሰባት ዳኞች በተሰየሙበት በሰበር ችሎት ከተሰጡ ውሳኔዎች መካከል ሰ/መ/ቁ 29181 [አመልካች የኢትዮጵ ንግድ ባንክ እና ተጠሪ እነ አቶ ልየው ቸኮል (2 ሰዎች) ታህሳስ 20 ቀን 2002 ዓ.ም. ቅጽ 10] 34329 [አመልካች የኢትዮጵ ንግድ ባንክ እና ተጠሪ እነ አቶ ፈቃደ ደምስስ (2 ሰዎች) ታህሳስ 20 ቀን 2002 ዓ.ም. ያልታተመ] 39362 [አመልካች እነ አቶ ንጉሴ ታምራት (6 ሰዎች) እና ተጠሪ በከልቻ ትራንስፖርት አክስዮን ማህበር ታህሳስ 12 ቀን 2002 ዓ.ም. ያልታተመ] እንዲሁም 42239 [አመልካች ብሔራዊ ማዕድን ኮርፖሬሽን ኃላ.የተ.የግል ኩባንያ እና ተጠሪ ዳኒ ድሪሊንግ ኃላ.የተ.የግል ኩባንያ ጥቅምት 29 ቀን 2003 ዓ.ም. ቅጽ 10] ይገኙበታል፡
ምንም ምክንያት የሌለው ውሳኔ
የሰበር ችሎት የሚሰጠው የህግ ትርጉም አስገዳጅነት በህግ የተወሰነ እንደመሆኑ የስር ፍርድ ቤቶች ቢያምኑበትም ባያምኑበትም መቀበልና ተፈጻሚ የማድረግ ግዴታ አለባቸው፡፡ ሆኖም በህግ መደንገጉ ብቻውን የሰበር ችሎት ውሳኔ በስር ፍርድ ቤቶች ሙሉ ተቀባይነትና ተፈጻሚነት ኖሮት ወጥነትና ተገማችነትን ለማስፈን ዋስትና አይሆንም፡፡ ስለሆነም የአስገዳጅነት ኃይል በህግ ብቻ ሳይሆን በአሳማኝነት ኃይል መታገዝ ይኖርበታል፡፡ ምክንያት የሌለው ብሎም ምክንያታዊ ያልሆነ ውሳኔ የአሳማኝነት ኃይል አይኖረውም፡፡ ይህ ደግሞ የስር ፍርድ ቤቶች ውሳኔውን እንዳላዩ በማለፍ ተቃራኒ ውሳኔ እንዲሰጡና ተመሳሳይ ጉዳዮች የችሎቱን በር እንዲያጣብቡ በር ይከፍታል፡
በፍርድ ቤት በሚሰጥ ውሳኔ ላይ በዋነኛነት የተያዘውን ጭብጥ፤ ጭብጡ እንዴት እንደተወሰነና የተወሰነበትን ምክንያት መግለጽ አለበት፡፡ [የፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ 182(1)] ምክንያት የሌለው ውሳኔ መሰረታዊ ጉድለት አለበት፡፡ በተለይ በሰበር ችሎት የሚሰጥ ውሳኔ ሁልጊዜም ቢሆን ምክንያት ሊኖረው ይገባል፡፡ ችሎቱ ምክንያት መስጠት ያለበት የስር ፍርድ ቤትን ውሳኔ ሲሽር ብቻ አይደለም፡፡ ውሳኔውን ለማጽናትም ምክንያት ያስፈልጋል፡፡
ይህንን የውሳኔ አጻጻፍ መርህና ስርዓት በሚጣረስ መልኩ የሰበር ችሎት በሰ/መ/ቁ 27162 (አመልካች ወ/ሮ እሸት መሐመድ እና ተጠሪ ዘይነባ አህመድ ጥቅምት 25 ቀን 2001 ዓ.ም. ያልታተመ) የሰጠው ውሳኔ እንደሚከተለው ይነበባል፡፡
“ለዚህ ችሎት ጥቅምት 23 ቀን 1999 ዓ.ም በተፃፈ ማመልከቻ የቀረበው የሰበር አቤቱታ ለተጠሪ ደርሶ ሐምሌ 2ዐ ቀን 1999 ዓ.ም. የተፃፈ የመልስ ማመልከቻ አቅርቧል፡፡
የግራ ቀኙን ክርክር አቤቱታው ከቀረበበት ውሣኔ መደምደሚያና ለዚህም መሠረት ከሆነው የሕግ ትንታኔ አንፃር ተመርምሮ ውሣኔው ጉድለት የሌለበት ሆኖ ስለተገኘ በከፍተኛ ፍ/ቤት በመዝገብ ቁጥር 41534 በሐምሌ 17 ቀን 1998 ዓ.ም የተሰጠው ውሣኔ በፍ/ብ/ስ/ስ/ሕግ 348/1/ መሠረት ፀንቷል፡፡ ይፃፍ ግራ ቀኙ ኪሣራቸውን ለየራሣቸው ይቻሉ፡፡ መዝገቡ ተዘግቷል፡፡ ይመለስ፡፡”
ከዚህ ውሳኔ ጋር ተመሳሳይነት ባለው መልኩ በሰ/መ/ቁ 39403 [አመልካች እነ ወ/ሮ ሄርሜላ ውድነህ እና ተጠሪ መሠረት ሀብታሙ ሐምሌ 3 ቀን 2003 ዓ.ም. ያልታተመ] ፤ 24515 [አመልካች እነ አቶ ሐብቴ ዙርጋ እና ተጠሪ እነ አቶ ሙሉሸዋ ተፈራ ጥቅምት 20 ቀን 2001 ዓ.ም. ያልታተመ] ፤ 16239 [አመልካች እነ አቶ ኃይሉ ቶላ እና ተጠሪ አቶ ግርማ ሁሪሣ ታህሳስ 26 ቀን 1999 ዓ.ም. ያልታተመ] ፤ 16614 [አመልካች ኢስት አፍሪካ ቦትሊንግ ኃ/የተ/የግ/ማ/ እና ተጠሪ እነ አቶ ተዘራ ዘለቀ ኃዳር 28 ቀን 1999 ዓ.ም. ያልታተመ] ፤ እና 16842 [አመልካች አቶ ተሰማ ዘረፋ እና ተጠሪ አቶ አብሴ ዓለሙ ወራሾች ታህሳስ 19 ቀን 1999 ዓ.ም. ያልታተመ] ፤ አንዳችም ምክንያት ሳይቀርብ ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡
በጣም የሚገርመው የውሳኔዎቹ ምክንያት አልባነት ብቻ ሳይሆን ከግማሽ ገጽ የምታንስ ውሳኔ ለመጻፍ ከአንድ ዓመት እስከ ሶስት ዓመት መፍጀቱ ነው፡፡ በውሳኔዎቹ ላይ አቤቱታ የቀረበበትና ውሳኔ የተሰጠበት ቀን ያለው ልዩነት ትንሹ አንድ አመት ሲሆን ትልቁ ደግሞ ሶስት ዓመት ነው፡፡ ሌላው አስገራሚው ነገር ደግሞ የሰ/መ/ቁ 24515 ሶስት ለሁለት በሆነ አብላጭ ድምጽ የተሰጠ ሲሆን ጥልቅ በሆነ የህግ ትንተና ተደግፎ አስር ገጽ የልዩነት ሓሳብ በውሳኔው ላይ ሰፍሯል፡፡ የዚህ ልዩነት ተገላቢጦሹ ደግሞ በሰ/መ/ቁ 3915 [አመልካች የኢትዮ/አየር መንገድ እና ተጠሪ አቶ እንደርታ መስፍን ሚያዝያ 22 ቀን 2002 ዓ.ም. ያልታተመ] ታይቷል፡፡ በዚህ መዝገብ የስር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ አራት ለአንድ በሆነ አብላጨ ድምጽ የተሻረ ሲሆን አነስተኛው ድምጽ ለመለየት የሰጠው ምክንያት “የስር ፍ/ቤቶች የሰጡት ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ባለመሆኑ…” የሚል ነው፡፡ በእርግጥ ይህ ምክንያት አይደለም፡፡ የምክንያት አለመኖር እንጂ፡
በቅጽ ውስጥ ያልተካተቱ (ያልታተሙ) ውሳኔዎች
የሰበር ችሎት ውሳኔ ቀላልና አመቺ በሆነ መንገድ ለስር ፍርድ ቤቶች እንዲደርስ ካልተደረገ በተመሳሳይ ጉዳዮች ላይ ጥራትና ወጥነት ያለው ፍርድ አይኖርም፡፡ የፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅን እንደገና ለማሻሻል የወጣው አዋጅ ቁ 454/1997 አንቀጽ 2(1) የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስገዳጅ የህግ ትርጉም የተሰጠባቸውን ውሳኔዎች በየደረጃው ላሉ ፍርድ ቤቶችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት አሳትሞ እንደሚያሰራጭ ይደነግጋል፡፡ ይህ በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ላይ የተጣለው ግዴታ ከሰበር ውሳኔ አስገዳጅነት ጋር በተያያዘ አከራካሪ ጥያቄ ያስነሳል፡፡ እስከአሁን ድረስ የፌ/ጠ/ፍ/ቤት አስገዳጅ የህግ ትርጉም የተሰጠባቸውን ውሳኔዎች በአስራ ስድስት ቅጾች አሳትሞ አሰራጭቷል፡፡ ሆኖም ቅጾቹ ሁሉንም የሰበር ውሳኔዎች ያካተቱ አይደለም፡፡ ይህ ደግሞ በቅጽ ውስጥ ያልተካተቱ (ያልታተሙ) ውሳኔዎች በአዋጁ መሰረት አስገዳጅ ናቸው? የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡
እስካሁን ድረስ ጥያቄው በሰበር ችሎት የህግ ትርጉም አልተሰጠውም፡፡ ሆኖም ችሎቱ ራሱ ያልታተሙ ውሳኔዎችን ሲጠቅስ ይስተዋላል፡፡ የሰ/መ/ቁ 44218 [አመልካች የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን እና ተጠሪ እነ አቶ ታጁ አባጋሮ (21 ሰዎች) ግንቦት 13 ቀን 2003 ዓ.ም. ቅጽ 9] ችሎቱ በሰ/መ/ቁ 43197 የሰጠውን አስገዳጅ የህግ ትርጉም ይጠቅሳል፡፡ ሆኖም 43197 በቅጽ ውስጥ የለም፡፡ በሰ/መ/ቁ. 39580 [አመልካች አልታቤ ኮሌጅ እና ተጠሪ ሠይድ መሐመድ ግንቦት 18 ቀን 2001 ዓ.ም ያልታተመ] እንዲሁ ችሎቱ የሰ/መ/ቁ 39579ን በመጥቀስ ውሳኔ የሰጠ ቢሆንም የሰ/መ/ቁ 39579 በቅጾቹ ውስጥ አልተካተተም፡፡ በተመሳሳይ መልኩ ችሎቱ በሰ/መ/ቁ 42901 (ቅጽ 8) ላይ በሰ/መ/ቁ 40055 የሰጠውን ተመሳሳይ የሕግ ትርጉ የሚጠቅስ ቢሆንም ይህ የተጠቀሰው የሰበር ውሳኔ በቅጾቹ ውስጥ አልተካተም፡፡ የችሎቱ አካሄድ በቅጽ ያልተካተተ ውሳኔ የአስገዳጅነት ኃይል እንዳለው የተቀበለው ይመስላል፡፡
ወደኋላ ተመልሶ ስለመስራት (retro-activity)
የሰበር ውሳኔ አስገዳጅ መሆን የሚጀምረው ከመቼ ጀምሮ ነው? የሰበር ውሳኔ በትርጉም የሚፈጠር ራሱን የቻለ ህግ ነው፡፡ በተወካዮች ምክር ቤት የሚወጣ አዋጅና በሚኒስትሮች ምክር ቤት የሚወጣ ደንብ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ ተፈጻሚነት ያገኛል፡፡ በመርህ ደረጃ ህግ ወደ ኋላ ተመልሶ አይሰራም፡፡ በተለይ በወንጀል ህግ ይህ መርህ ህገ መንግስታዊ መሰረት ያለው ነው፡፡ በፍትሐ ብሔር ጉዳይም ቢሆን ቀድመው የተከናወኑ ህጋዊ ተግባራት ውጤትና አፈጻጸም ብዙውን ገዚ በ’መሸጋገሪያ ድንጋጌዎች’ በግልጽ ተለይቶ ይወሰናል፡፡
የሰበር ውሳኔ እንደ ማናቸውም የፍርድ ቤት ውሳኔ ሁሉ ተጽፎና በአስቻሉት ዳኞች ተፈርሞ ለተከራካሪ ወገኖች በይፋ ከተነበበት ቀን ጀምሮ የጸና (ውጤት ያለው) ይሆናል፡፡ [ፍ/ስ/ስ/ህ/ቁ 181(1)] ሆኖም የሰበር ውሳኔ በተከራካሪ ወገኖች ላይ ከሚኖረው ውጤት በተጨማሪ በስር ፍርድ ቤቶችም ላይ የአስገዳጅነት ውጤት አለው፡፡ በስር ፍርድ ቤቶች ላይ አስገዳጅነቱ መቼ እንደሚጀምር ራሱን የቻለ የህግ ትርጉም የሚፈልግ ጥያቄ ነው፡፡ ጥያቄው በዋነኛነት በውሳኔው መታተምና አለመታተም ላይ ያጠነጥናል፡፡ በዚህ ነጥብ ላይ በሰበር ችሎት የተሰጠ የህግ ትርጉም ባይኖርም ከላይ በቅጽ ውስጥ ያልተካተቱ ውሳኔዎች አስመልክቶ እንዳየነው ያልታተመ ውሳኔ በችሎቱ ሳይቀር መጠቀሱ ህትመት ቅድመ ሁኔታ ስላለመሆኑ ተቀባይነት አግኝቷል ለማለት እንችላለን፡፡ ስለሆነም የሰበር ችሎት ውሳኔ በይፋ ከተሰጠበት ቀን ጀምሮ አስገዳጅነት ይኖረዋል ብሎ መደምደም የሚያስኬድ ነው፡፡
የሰበር ውሳኔ አስገዳጅነት ወሰኑ በስር ፍርድ ቤቶች ላይ የተገደበ ነው፡፡ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ እንደሚወጣ ህግ በማናቸውም የፌደራል ወይም የክልል ህግ አውጪና አስፈጻሚ እንዲሁም ማንኛውም የተፈጥሮ ሰውና በህግ የሰውነት መብት በተሰጠው አካል [የፌደራል ነጋሪት ጋዜጣ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁ 3/1987 አንቀጽ 2(3)] ላይ አስገዳጅነት የለውም፡፡ አስገዳጅነቱ በስር ፍርድ ቤቶች ላይ ብቻ መሆኑ ወደ ኋላ ተመልሶ ከመስራት ጋር በተያያዘ ሁለት መሰረታዊ ቁምነገሮች ያስጨብጠናል፡፡
ይኸውም፤
- አንደኛ የሰበር ችሎት ውሳኔ ከሰጠበት ጋር ተመሳሳይ የሆነ ጉዳይ በማናቸውም ደረጃ በሚገኝ ፍርድ ቤት ላይ በክርክር ላይ በሚገኝበት ጊዜ ሁሉ አስገዳጅነት ይኖረዋል፡፡ ለክርክሩ መነሻ የሆነው ጉዳይ ሰበር ውሳኔ ከመስጠቱ በፊት የተፈጸመ ቢሆንም ክርክሩን ለመፍታት አስገዳጅነት አለው፡፡ ክርክሩ የሰበር ውሳኔ ከተሰጠበት ቀን በፊት ተጀምሮ ሊሆን ይችላል፡፡ ወይም ደግሞ በሰበር አስገዳጅ የህግ ትርጉም የተሰጠው ጉዳዩ በመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ውሳኔ አግኝቶ በይግባኝ ክርክር ጊዜ ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚያም አልፎ ጉዳዩ በክልል ሰበር ሰሚ ችሎት እየታየ ባለበት ወቅት ለጉዳዩ አግባብነት ያለው አስገዳጅ የህግ ትርጉም ከተሰጠ ተፈጻሚነት ይኖረዋል፡፡ በሰመ/ቁ 84353 (አመልካች ጥቁር አባይ ኮንስትራክሽን አ/ማህበር ሂሣብ አጣሪ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ባለአደራ ቦርድ እና ተጠሪ ወጋገን ባንክ አ/ማህበር ጥር 2 ቀን 2005 ዓ.ም. ቅጽ 14) መካከል በነበረው ክርክር ተጠሪ ለተያዘው ጉዳይ ካቀረባቸው ክርክሮች አንዱ ፍርድ ቤት ባንክ ለብድር መክፈያ በያዘው ንብረት ላይ የሚካሄድ ሐራጅ እንዲቆም ወይም እንዲፈርስ በሚል የሚቀርብን ክስ አይቶ የመዳኘት ስልጣን እንደሌለው የሰበር ችሎት በሰ/መ/ቁ 70824 አስገዳጅ የህግ ትርጉም መስጠቱን የሚጠቅስ ሲሆን አመልካች በበኩሉ ለክርክሩ መነሻ የሆነው ሐራጅ የሰበር ችሎት የህግ ትርጉም ከመስጠቱ ከአምስት ቀናት በፊት የተደረገ በመሆኑ የሰበር ሰሚው ትርጉም ወደ ኋላ ተመልሶ ሊሰራ አይገባም በማለት ተከራክሯል፡፡ ችሎቱ የአመልካችን ክርክር ያልተቀበለው ሲሆን ወደ ኋላ ተመልሶ መስራትን አስመልክቶ በሐተታው እንዳሰፈረው አስገዳጅነት ያለው የህግ ትርጉም “…ተፈጻሚነቱ በተመሣሣይ ጉዳይ በሌሎች ወገኖች ክርክር በተፈጠረበት ጊዜ ይህንኑ አስመልክቶ በሰበር ሰሚ ችሎት የተሰጠ ትርጉም አለ ወይስ የለም ከሚለው ነጥብ አንጻር ታይቶ ተፈጻሚ የሚሆን እንጂ ትርጉም የተሰጠበትንና የክርክር ምክንያት የሆነው ነገር መቼ ተፈጸመ…ከሚለው የጊዜ ቅደም ተከተል አንጻር እየታየ የሚፈጸም” አይደለም፡፡
- ሁለተኛ አስገዳጅ የህግ ትርጉም ክርክሩ ተቋጭቶ ውሳኔ ባገኘ ጉዳይ ላይ ወደ ኋላ ተመልሶ አይሰራም፡፡ ውሳኔ ያገኘ ጉዳይ በይግባኝ እስካልተሻረ ድረስ የተሳሳተም ቢሆን ተፈጻሚነት አለው፡፡ ውሳኔው መሰረታዊ የህግ ስህተት እንደተፈጸመበት ከጊዜ ኋላ በተሰጠ አስገዳጅ የህግ ትርጉም ግልጽ ሆኖ ቢታይም ትርጉሙ ውሳኔውን የማሻር ውጤት የለውም፡፡ የሰበር ችሎት ራሱ የሰጠውን የህግ ትርጉም በሚለውጥበት ጊዜም የተሻረውን የህግ ትርጉም መሰረት በማድረግ የተሰጠ የስር ፍርድ ቤት ውሳኔ እንደጸና ይቆያል፡፡ የአዋጅ ቁ 457/97 ዓይነተኛ ዓላማ፤
“…ውሳኔ የሚያሻቸው ጉዳዮች ዓይነት ከዚህ በፊት በፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ችሎት ቀርበው ትርጉም ተሰጥቶባቸው ከሆነ በሀገሪቱ ወጥ የሆነ የሕግ አተረጓጎምና አፈጻጸም ማስፈን እንዲቻል በተመሣሣይ ታይተው እንዲወሰኑ ለማድረግ እንዲቻል እንጂ ሥርዓቱን አሟጦ በውሳኔ የተቋጨን ጉዳይ ሁሉ እንደገና እየቀሰቀሱ የተረጋጋውን ሁኔታ ለማናጋት ወይም ተከራካሪ ወገኖችን ተገማች ላልሆነ የዳኝነት ስርዓት ለመጋበዝ ተፈልጎ አይለም፡፡”
(አመልካች አቶ ጌታቸው ደያስ (ሁለት ሰዎች) እና ተጠሪ ወ/ሮ ሩቅያ ከድር መጋቢት 12 ቀን 2004 ዓ.ም. ሰ/መ/ቁ 68573 ቅጽ 13)
የህግ ትርጉም መለወጥ
የሰበር ውሳኔ አስገዳጅነቱ ለስር ፍርድ ቤቶች እንጂ ለራሱ ለችሎቱ አይደለም፡፡ ችሎቱ በሌላ ጊዜ በተመሳሳይ ጭብጥ የተለየ ትርጉም ሊሰጥ ይችላል፡፡ ምንም እንኳን የሰበር ችሎቱ በሌላ ጊዜ በተመሳሳይ ጭብጥ የተለየ ትርጉም መስጠት ቢችልም በጠባቡ ካልተተገበረ የሰበር ውሳኔ በስር ፍርድ ቤቶች ሊኖረው የሚገባውን የተሰሚነትና የተቀባይነት ደረጃ በእጅጉ ዝቅ ያደርገዋል፡፡ መረሳት የሌለበት ነገር ወጥነት ለስር ፍርድ ቤቶች ብቻ ሳይሆን ለራሱ ለችሎቱም በእጅጉ ያስፈልገዋል፡፡ በአንድ ጭብጥ ላይ በየጊዜው የሚቀያየር የሰበር ውሳኔ በስር ፍርድ ቤቶች ዘንድ ተፈጻሚነቱ አጠያያቂ ነው፡፡ ስለሆነም በአንድ ጭብጥ ላይ ወዲያው ወዲያው በሰበር ችሎት የአቋም ለውጥ በሚኖር ጊዜ የስር ፍርድ ቤቶችን ከማደናገሩም በላይ የውሳኔውን የተሰሚነት ደረጃ ዝቅተኛ ያደርገዋል፡፡ በተመሳሳይ ጭብጥ የተለየ ትርጉም መስጠት እጅግ አስፈላጊ የሚያደርጉ ሁኔታዎች ወይም ምክንያቶች መኖራቸው እስካልተረጋገጠ ድረስ አንድ ጊዜ የተሰጠ ውሳኔ ፀንቶ ሊቆይ ይገባል፡፡ የተለየ ትርጉም ሲያስፈልግ ለውጥ ማድረግ የተፈለገበትን ምክንያት በአዲሱ ውሳኔ ላይ በግልጽ ማመልከትና የበፊቱን ውሳኔ በማያሻማ መልኩ በግልጽ መሻር ያስፈልጋል፡፡
በግልጽ የሚደረግ የትርጉም ለውጥ ያልተገባ ውዥንብርን ያስወግዳል፡፡ በአነስተኛ ወጪ ፍትሕ በቀላሉ እንዲሰፍንም ያደርጋል፡፡ የቀድሞ የህግ ትርጉም በግልጽ ቀሪ ተደርጎ አዲስ አቋም ከተያዘባቸው መዝገቦች መካከል ሰ/መ/ቁ 42239 [አመልካች ብሔራዊ ማዕድን ኮርፖሬሽን ኃላ.የተ.የግል ኩባንያ እና ተጠሪ ዳኒ ድሪሊንግ ኃላ.የተ.የግል ኩባንያ ጥቅምት 29 ቀን 2003 ዓ.ም. ቅጽ 10] ፤ 43821 [አመልካች ወ/ሮ ትርሐስ ፍስሐዬ እና ተጠሪ ወ/ሮ ዘነበች በሪሁን ጥር 5 ቀን 2002 ዓ.ም. ቅጽ 9 ] እና 36730 [አመልካች የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን እና ተጠሪ አቶ አማረ ገላው ሐምሌ 30 ቀን 2002 ዓ.ም. ቅጽ 9] ተጠቃሽ ናቸው፡፡ በሰ/መ/ቁ 36730 የግልግል ዳኝነት ጉባኤ የሚሰጠው ውሳኔ የመጨረሻ እንደሆነ ስምምነት ከተደረገ በሰበር ችሎት ሊታይ አይችልም በማለት በሰ/መ/ቁ 21849 ተሰጥቶ የነበረው የህግ ትርጉም ተሸሮ ችሎቱ የጉባኤውን ውሳኔ ለማየት ስልጣን እንዳለው ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡ በሰ/መ/ቁ 43281 ዳኝነት እንደገና እንዲታይ ጥያቄው መቅረብ ያለበት ይግባኝ ከመቅረቡ በፊት እንደሆነ በሰ/መ/ቁ 16624 ተሰጥቶ የነበረው የህግ ትርጉም ተለውጦ ከይግባኝ በኋላም ሊቀርብ እንደሚችል አቋም ተይዞበታል፡፡ የሰመ/ቁ 36730 የይርጋ ማቋረጫ ምክንያትን የሚመለከት ሲሆን ከዚህ ቀደም በሰ/መ/ቁ 16648 ስልጣን ለሌለው የዳኝነት አካል ክስ ማቅረብ የይርጋ ጊዜን እንደማያቋርጥ ተደርጎ ህጉ መተርጎሙ አግባብነት እንደሌለው ታምኖበት ይርጋን እንደሚያቋርጥ የህግ ትርጉም ተሰጥቶበታል፡፡
የትርጉም ለውጥ በተደረገባቸው ሶስቱም መዝገቦች ውሳኔ የተሰጠው ሰባት ዳኞች በተሰየሙበት ችሎት ነው፡፡ ይህም የትርጉም ለውጥ ከሚደረግበት ስርዓት ጋር በተያያዘ ጥያቄ እንድናነሳ ያስገድደናል፡፡ ሰባት ዳኞች በተሰየሙበት ችሎት የተሰጠ የህግ ትርጉም ከሰባት ያነሱ ለምሳሌ አምስት ዳኞች በተሰየሙበት ችሎት ሊለወጥ ይችላል? የዳኞች ቁጥር እንደተጠበቀ ሆኖ በሙሉ ድምጽ የተሰጠ ውሳኔ በአብላጭ ድምጽ ሊለወጥ የመቻሉ ጉዳይም ሌላው በጥያቄነት መነሳት ያለበት ነው፡፡
ሰበር ውሳኔ የሰጠበት ህግ ‘ሲሻር’ የውሳኔው የአስገዳጅነት ውጤት
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ችሎት ውሳኔ በስር ፍርድ ቤቶች ላይ የአስገዳጅነት ውጤት እንዲኖረው በህግ የተደነገገው በ1997 ዓ.ም. ሲሆን የሰበር ችሎት የዚህን አዋጅ መውጣት ተከትሎ በሰበር ስልጣኑ የሚሰጣቸው ውሳኔዎች በፌደራልና በክልል የስር ፍርድ ቤቶች ላይ የአስገዳጅነት ውጤት አግኝተዋል፡፡ ሆኖም በአዋጅ ቁ 454/1997 ላይ የድንጋጌ ለውጥ ሳይኖር የአንድ አዋጅን መሻር ተከትሎ በሰበር ትርጉም የተሰጠበት ውሳኔ የሚኖረው ህጋዊ ውጤት በህጉ አፈፃፀም ላይ በተግባር የሚያጋጥም ችግር ሆኗል፡፡
በእርግጥ ሰበር ትርጉም የሰጠበት ህግ ተሸሮ ትርጉም የተሰጠበት ድንጋጌም ቀሪ ወይም ውጤት የሌለው በሚሆንበት ጊዜ ውሳኔውም ያለ አንዳች ቅድመ-ሁኔታ ለቀጣይ ተመሳሳይ ጉዳዮች የአስገዳጅነት ውጤት ሊኖረው እንደማይችል ግልጽ ነው፡፡ ለምሳሌ አዋጅ ቁጥር 639/2001 ለባንክ ወይም ለአነስተኛ የፋይናንስ ተቋም ብድር መያዣነት የተሰጠ የማይንቀሳቀስ ንብረትን የሚመለከት ውል በፍርድ ቤት መዝገብ ወይም ስልጣን በተሰጠው አዋዋይ ፊት መፈረም እንደማያስፈልገው በመደንገግ በፍትሐ ብሔር ህግ ቁጥር 1723 ስር የተመለከተውን ቅድመ-ሁኔታ በከፊል ቀሪ አድርጎታል፡፡ ስለሆነም የሰበር ችሎት ከዚህ አዋጅ መውጣት በፊት የፍትሐ ብሔር ህግ ቁጥር 1723ን መሰረት በማድረግ ለባንክ ወይም ለአነስተኛ የፋይናንስ ተቋም ብድር መያዣነት የተሰጠ የማይንቀሳቀስ ንብረትን የሚመለከት ውልን በመተርጎም የሰጣቸው ውሳኔዎች በስር ፍርድ ቤቶች የአስገዳጅነት ውጤት አይኖራቸውም ማለት ነው፡፡
ይሁን እንጂ አንዳንድ ጊዜ አንድ አዋጅ ሙሉ በሙሉ ተሽሮ በአዲስ አዋጅ ሲተካ በተሻረው አዋጅና በአዲሱ አዋጅ የሚገኙ የተወሰኑ ድንጋጌዎች ምንም ዓይነት የይዘት ለውጥ አይደረግባቸውም፡፡ ለዚህ ጥሩ አብነት የሚሆነን የአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁጥር 42/85 በ377/96 መተካት ነው፡፡ ምንም እንኳን አዋጅ ቁጥር 42/85 በ377/96 የተሻረ ቢሆንም በቀድሞው አዋጅ ላይ የነበሩ ብዙ ድንጋጌዎች ምንም ዓይነት የይዘት ለውጥ አልተደረገባቸውም፡፡ ለምሳሌ የአዋጁን የተፈጻሚነት ወሰን የሚመለቱ ድንጋጌዎች፤ የስራ ውል አመሰራረትን የሚመለከቱ ድንጋጌዎች፤ የስራ ውል የሚቆይበትን ጊዜ አስመልክቶ የተቀመጡ ድንጋጌዎች (አዲስ ንዑስ አንቀጾች ከመጨመራቸው ውጪ የቀድሞ ድንጋጌዎች አልተቀየሩም) እንዲሁም ሌሎች ብዙ ድንጋጌዎች ይዘታቸው አልተቀየረም፡፡
እዚህ ላይ ጥያቄ ይነሳል፡፡ የይዘት ለውጥ ባልተደረገበት አንቀጽ ላይ አዋጅ ቁጥር 42/85ን መሰረት በማድረግ በሰበር የተሰጠ ውሳኔ አዋጁ በ377/96 ከተሻረ በኋላም የአስገዳጅነት ውጤት አለው? በዚህ ነጥብ ላይ የሰበር ችሎት በሁሉም ዓይነት የስራ ክርክር፤ የፍትሐብሔር፤ የወንጀልና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ወጥ በሆነ መልኩ ተፈፃሚነት ያለው ውሳኔ ያልሰጠ ቢሆንም የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይን በተመለከተ ግን በከፊልም ቢሆን ምላሽ ሰጥቶበታል፡፡ ስለሆነም በአዋጅ ቁጥር 42/85 መሰረት የተሰጠ የሰበር ውሳኔ አዋጅ ቁጥር 377/96 ከወጣ በኃላ በአዲሱ አዋጅ መሰረት የሚነሱ የስራ ክርክሮች ላይ የሚኖረውን ህጋዊ ውጤት በከፊልም ቢሆን ምላሽ ያገኘ ይመስላል፡፡
በአመልካች ሐመረ ወርቅ ቅ/ማሪያም ቤተክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤት እና መልስ ሰጭዎች እነ ዲያቆን ምህረተ ብርሐን (6 ሰዎች) (ግንቦት 4 ቀን 1998 ዓ.ም ሰ/መ/ቁ 18419 ቅጽ 8) በነበረው የአሰሪና ሰራተኛ ክርክር ሰበር ችሎቱ የተያዘውን ጉዳይ ብቻ አስመልክቶ እንዳለው አዋጅ ቁጥር 42/85 በአዋጅ ቁጥር 377/96 የተሻረ ቢሆንም ነጥቡን በሚመለከት ሁለቱ አዋጆች አንድ አይነት ድንጋጌዎችን የያዙ በመሆኑ ችሎቱ የአዋጅ ቁጥር 42/85 ድንጋጌዎችን መሰረት አድርጎ በተጠቀሰው ነጥብ ላይ የሰጠው የህግ ትርጉም ለአዋጅ ቁጥር 377/96 ድንጋጌዎችም አግባብነት ያለው ነው፡፡
Filed under: Articles, Case Comment, Uncategorized
