ትርጓሜ
በሟች ንብረት ላይ መብት አለን የሚሉትን ወገኖችን ወይም ወራሾችን የመወሰን፣ የሟች ኑዛዜ መኖር አለመኖሩን የማረጋገጥና በኑዛዜው ተጠቃሚዎችን የመለየት፣ ውርሱን የማስተዳደር የውርሱን ተከፋይ ገንዘብ የመሰብሰብና እዳዎችን የመክፈል፣ የሟች ንብረት ማጣራትና ማፈላለግ እንዲሁም የኑዛዜ ስጦታዎችን የመክፈል ሥልጣን ያለውና እነዚህ ተግባራት እንዲያከናውን በወራሾች ወይም በፍርድ ቤት የሚሾም አጣሪ
ሰ/መ/ቁ. 45905 ቅጽ 11፣[1] ፍ/ህ/ቁ. 944፣ 946፣ 956፣ 960
የአጣሪው ስልጣን ወሰን
በፍ/ብ/ሕ/ቁ. 956 እንደተደነገገው የአጣሪው ሥራ ሟቹ አንድ ኑዛዜ ትቶ እንደሆነ መፈለግና በመጨረሻ ውርሱ የሚደርሳቸው ሰዎች እነማን እንደሆኑ ማረጋገጥ፣ የውርሱን ሃብት ማስተዳደር፣ መክፈያቸው የደረሰውን የውርስ እዳዎች መክፈል እና ሟቹ በኑዛዜ ያደረጋቸውን ስጦታዎች መክፈልና የኑዛዜውን ቃል ለመፈፀም ማንኛቸውም ሌሎች አስፈላጊ ጥንቃቄዎች ማድረግ ነው፡፡ እነዚህ ከዚህ በላይ የተዘረዘሩትን ተግባራት በሚያከናውንበት ጊዜ ደግሞ በኑዛዜው የውርስ ንብረት መሆናቸው ተጠቅሶ የክፍፍል ስርአትም የተቀመጠላቸውና ወራሾች በሙሉ የተስማሙባቸው ንብረቶችና መክፈያቸው የደረሰው የውርስ እዳዎች ሲኖሩ በወራሾቹ ስምምነት መሰረት ንብረቶቹን ሊያከፋፍልና እዳዎችንም ሊከፍል ይችላል፡፡
በኑዛዜው ላይ በተጠቀሱትና ባልተጠቀሱት ንብረቶች የውርስ ሃብት መሆን ያለመሆን ላይ ወራሾቹ ያልተስማሙና ክርክር ያነሱ ከሆነ ግን የአጣሪው ሥራና ሐላፊነት ወራሾች የተስማሙባቸውን ንብረቶች የውርስ ሃብት መሆናቸው መመዝገብ፣ ወራሾች ያልተስማሙባቸው ንብረቶችና እዳዎች ካሉ ደግሞ ማስረጃ በመሰማት ማስረጃው ምን እንደሚያስረዳ ሪፖርቱ ላይ በማስፈር እንዲያጣራ ላዘዘው ፍ/ቤት ማቅረብ እንጂ ንብረት አጣሪው ይህ ንብረት የውርስ ሐብት አይደለም የሚሉ ወራሾች ቢኖሩ ማስረጃ በመስማት የውርስ ሃብት መሆኑን ስለተገነዘብኩኝ ንብረቱ የውርስ ሃብት ነው በማለት ወስኛለሁ ወይም ደግሞ ማስረጃውን እንደተመለከትኩት ንብረቱ የውርስ ሐብት ያለመሆኑን ስላረጋገጥኩኝ የውርስ ሐብት አይደለም በማለት ወስኛለሁ ለማለት የሚያስችለው ሥልጣን የለውም፡፡
ሰ/መ/ቁ. 23322 ቅጽ 7፣[2] ፍ/ህ/ቁ. 956
የዳኝነት ስልጣን
የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤቶች የወራሽነት የምስክር ወረቀት ከመስጠት በስተቀር ውርስ እንዱጣራ አጣሪ የመሾም የስረ ነገር ሥልጣን የላቸውም፡፡
ሰ/መ/ቁ. 52530 ቅጽ 11፣[3] ሰ/መ/ቁ. 35657 ቅጽ 9፣[4] አዋጅ ቁ. 361/95 አንቀጽ 41/ለ/ሸ/፣ አዋጅ ቁጥር 408/96
በአብላጫ ድምጽ የተሰጡ
የውርስ አጣሪ ሪፖርት
የውርስ አጣሪው የማጣራቱን ተግባር ከአከናወነ በኋላ ለወራሾችና ለፍርድ ቤት የሚያቀርበው ሪፖርት
በውርስ ሃብት ክፍፍል ረገድ እንደውሳኔ የሚቆጠረው የውርስ አጣሪ ሪፖርት ሳይሆን፣ ሪፖርቱ በሕጉ መሠረት የቀረበ ነው በሚል በፍ/ቤት የሚሰጠው ውሳኔ ነው፡፡
ሰ/መ/ቁ 44038 ያልታተመ[5]
የውርስ አጣሪ ሪፖርት በፍርድ ቤት መጽደቅ በራሱ ፍርድ ሁኖ ለአፈፃፀም የሚቀርብ ሣይሆን እንደማስረጃ የሚያገለግል ነው፡፡
ሰ/መ/ቁ. 45905 ቅጽ 11፣[6] ፍ/ህ/ቁ. 944፣ 946፣ 956፣ 960
[1] አመልካች ሚስስ ሚላን ፑሲጂ /2 ሰዎች/ እና ተጠሪ እነ ሐንድሬ ፒስ ማልጂ /2 ሰዎች/ ጥቅምት 3 ቀን 2003 ዓ.ም.
[2] አመልካች ወ/ሮ አዳነች ወርዶፋ እና ተጠሪዎች እነ ወ/ሮ አስናቀች ወርዶፋ ሰኔ 19 ቀን 2000 ዓ.ም.
[3] አመልካች እነ አቶ ሰናይ ልዑልሰገድ /2 ሰዎች/ እና ተጠሪ እነ ወ/ሮ ትእግስት ኃይሌ ኅዳር 14 ቀን 2003 ዓ.ም.
[4] አመልካቾች እነ ወ/ሮ እመቤት መክብብ እና ተጠሪ አቶ በድሉ መክብብ ጥቅምት 06 ቀን 2001 ዓ.ም.
[5] አመልካቾች እነ ጌታቸው ደስታ /2 ሰዎች/ እና ተጠሪ በላይ መለሰ የካቲት 9 ቀን 2002 ዓ.ም.
[6] አመልካች ሚስስ ሚላን ፑሲጂ /2 ሰዎች/ እና ተጠሪ እነ ሐንድሬ ፒስ ማልጂ /2 ሰዎች/ ጥቅምት 3 ቀን 2003 ዓ.ም.
Filed under: Articles, Case Comment
