Quantcast
Channel: Ethiopian Legal Brief
Viewing all articles
Browse latest Browse all 992

የችሎት ቀልዶችና ገጠመኞች #3

$
0
0

ከዚህ በታች የቀረቡት ገጠመኞችና ቀልዶች ከሶስት ዓመት በፊት በዘጋሁት በላልበልሃ የተባለ ብሎግ ላይ የወጡ ሲሆን አሁን ላይ አዳዲስ ስራዎች ተጨምረውባቸው በመጽሐፍ መልክ ታትመው ወጥተዋል፡፡ የመጽሐፉ ርዕስ ህግ ቀልድና ቁምነገር የሚል ሲሆን በ36 ብር በሜጋ የመጻህፍት መሸጫና ማከፋፈያ፣ በዩኒቨርሳል የመጽሐፍት መደብር እንዲሁም አዲስ አበባ ላይ በሌሎች መጽሐፍት መደብሮች ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

የጠበቃ ቀልዶች

ወይኔ አባዬ

አንድ ጠበቃ በአንዲት ትንሽ የገጠር ከተማ የገጠሩን ውበት እያደነቀ ይንሸራሸር ነበር፡፡ ትንሽ መንገድ ከሄደ በኋላ ከመንገዱ ጠርዝ ላይ አደጋ የደረሰ በሚመስል መልኩ ሰዎች ተሰብስበው ግርግር ሲፈጥሩ ይመለከታል፡፡ ወዲያውኑ በዛ ቦታ ላይ የመኪና አደጋ እንደደረሰ የጠበቃ ቀልቡ ከነገረው ነገር ተነስቶ ድምዳሜ ላይ ደረሰ፡፡ በአደጋው ቦታ ዙሪያ ወደተሰበሰቡት ሰዎች በመጠጋት የአደጋውን ዓይነትና ሁኔታ ለማጣራት ቢንጠራራም መግቢያ ቀዳዳ አላገኘም፡፡ በዚህ ጊዜ ፈጣን የጠበቃ ብልጠቱን በመጠቀም ዘዴ ቀየሰና “ወይኔ አባዬ! አሳልፉኝ! ወይኔ አባዬ! አባዬ!” እያለ ሲጮህ ወለል ብሎ ተከፈተለት፡፡ በግጭቱ ክፉኛ የተጎዳው አህያ አስፓልቱ ዳር ተዘርሮ እያቃሰተ ነበር፡፡

የኪስ ምስጋና

አንዲት ሴት በጣም ያስቸገራትን የፍርድ ቤት ሙግት ወደ አሸነፈላት ጠበቃ ዘንድ ትሔድና በደስታ ተውጣ “እንዴት አድርጌ እንደማመሰግንህ አላውቅም!” ትለዋለች፡፡ ጠበቃውም “ግብጾች ገንዘብን ከፈጠሩበት ጊዜ አንስቶ ለጥያቄሽ አንድና አንድ መልስ ብቻ ነው ያለው!” ሲል እቅጩን ነግሯታል፡፡

የችሎት ቀልዶች

ፍትሐዊ ጉቦ

የተከበሩት ዳኛ በጥቁሩ ካባቸው ደምቀው በችሎት አስከባሪ ፖሊስ ታጅበው ወደ ችሎት ሲገቡ ፖሊሱ ገና “አንዴ ተነሱ!” ብሎ ተናግሮ ሳይጨርስ በአዳራሽ የነበረው ሁሉ ብድግ ብሎ አከበራቸው፡፡ “ተቀመጡ!” አሉና የመጀመሪያውን መዝገብ ገልጠው ከሳሽና ተከሳሽን ተጣሩ፡፡ በመቀጠል የግራ ቀኙ ጠበቆች ብድግ ብለው በየተራ ስማቸውን አስመዘገቡ፡፡

ዳኛው በችሎት አዳራሽ የተሰበሰበውን ባለጉዳይ አንዴ አየት አደረጉና ወደ ጠበቆቹ ዞረው በትኩረት እየተመለከቱ “በዚህ ጉዳይ የከሳሽና የተከሳሽ ጠበቆች የሰጣችሁን ጉቦ ደርሶኛል” በማለት ተናገሩ፡፡ ይሄኔ ጠበቆቹ በሐፍረት እርስ በእርስ መተያየት ጀመሩ፡፡

“የከሳሽ ጠበቃ የሰጠኝ 15 ሺ ብር ሲሆን የተከሳሽ ጠበቃ ደግሞ 10 ሺ ብር ሰጥቶኛል፡፡” ዳኛው ይህን ከተናገሩ በኋላ ከኪሳቸው ቼክ አውጥተው ለከሳሽ ጠበቃ የሚከፈል 5 ሺ ብር ከጻፉ በኋላ “የከሳሽ ጠበቃ 5 ሺ ብር እላፊ ሰጥተኸኛል፡፡ እንካ ቼኩን ተቀበል፡፡” ብለው ቼኩን ሰጡት፡፡ ጠበቃው እያላበው ቼኩን ተቀበለ፡፡

በመጨረሻም ዳኛው ፊታቸው ላይ እፎይታና እርጋታ እየተነበበ እንዲህ አሉ፡፡

“አሁን ችሎቱ የእናንተን ጉዳይ ያለ አድልዎ ገለልተኛ ሆኖ ማየቱን ይቀጥላል፡፡”

የቀበጡ ዕለት

ምስክር ሆኖ የቀረበው ግለሰብ የዳኛው የችሎት አመራር ብዙም አልተመቸውም፡፡ እናም ለሚቀርብለት ጥያቄ ጠማማ መልስ እየሰጠ ዳኛውን ትንሽ ‘ሊያስነቅላቸው’ ዳዳው፡፡

ዳኛ——“ስምህ ማነው?”

ምስክር——“ማሙሽም ማሙሸትም ብለው ይጠሩኛል”

ዳኛ——“ዕድሜህ ስንት ነው?”

ምስክር——“አርባም ሃምሳም ይሆነኛል”

ዳኛ——“የት ነው የምትኖረው?”

ምስክር——“እዚህም እዚያም”

ዳኛ——“ምንድነው የምትሰራው?”

ምስክር——“ይሄንንም ያንንም”

የተከበሩት ዳኛ የምር ትዕግስታቸው አለቀ፡፡ “አስገቡት!” አሉና ከረር ያለ ትዕዛዝ ሰጡ፡፡ በገዛ ምላሱ ዘብጥያ መውረዱ እንደማይቀርለት የተረዳው ምስክር ድንጋጤ እየተሰማው “ቆይ! መቼ ነው የምወጣው?” ሲል መልሶ ጠየቀ፡፡

ዳኛ——“በቅርቡ ወይም አንድ ቀን!”

የችሎት ገጠመኞች

ሳቅ በሳቅ

“እኔ ላንቺ አንቺ ለእኔ!” ተባብለው የተጋቡ ባልና ሚስት ነፋስ መሃላቸው ገባና “አይንሺን ላፈር አይንህን ላፈር!” ተባብለው በፍቺ ተለያዩ፡፡ ቀጥሎ በጋራ ያፈሩትን መኖሪያ ቤት እኩል   በዓይነት ተካፈሉ፡፡ ሚስት ቤቱን አድሳ ወደ ሆቴል ቀየረችው፡፡ የሆቴሉንም ስም “ሳቅ በሳቅ ሆቴል” አለችው፡፡ ትንሽ ቆይቶ ባልም በተራው ቤቱን አድሶ ሆቴል ከፈተ፡፡ ለሆቴሉ ያወጣለት ስም “ደም ሳቂ ሆቴል” የሚል ነበር፡፡

ችሎቱ ወዶሻል

እውነተኛነቱ ያልተረጋገጠ አንድ የችሎት ገጠመኝ እንዲህ ይነበባል፡፡ ተከሳሽ ሆና የቀረበችው ሴት መልኳ የሚማርክ ሰውነቷ የሚያማልል ዓይነት ነበረች፡፡ በዛ ላይ የለበሰችው ጉርድ ቀሚስ ተደማምሮ የዳኛውን ቀልብ ሳትስብ አልቀረችም፡፡ በችሎት የሚከናወነው አጭር የቃል ክርክር እንዳበቃ ከሳሽና ተከሳሽ ከችሎት (ጉዳዩ የሚታው በዳኛው ቢሮ ውስጥ ነበር፡፡) ሊወጡ ሲያመሩ ዳኛው ተከሳሽ ወደኋላ እንድትቀር ምልክት ይሰጧታል፡፡ ድንጋጤ የተሰማት ተከሳሽ የዳኛውን ትዕዛዝ ሳታቅማማ በመቀበል አቋቋሟን አሳምራ ተገትራ ቀረች፡፡ በዚህ ጊዜ ውበቷን ለማድነቅ ዕድል አጥተው የነበሩት ዳኛ “ችሎቱ ወዶሻል!’ በማለት አድናቆታቸውን በጨዋ ደንብ ገልፀዋል፡፡

መማር ደጉ

ምስክሩ ለችሎቱ የመግቢያ ጥያቄዎች ምላሽ እየሰጠ ነው፡፡ ስሙን፤ ዕድሜውን፤ መኖሪያ አድራሻውን ከተናገረ በኋላ ዳኛው “የትምህርት ደረጃ?” ሲሉ ጠየቁት

ምሰክር——“አቋርጫለው”

ዳኛ——“ከስንት?”

ምስክር——“ከ1ኛ ክፍል”


Filed under: law fun, Uncategorized

Viewing all articles
Browse latest Browse all 992

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>