ብዙዎቻችሁ የEthiopian Legal Brief ጎብኚዎች wordpress.com ላይ በላልበልሃ የሚል ብሎግ እንዳለኝ የምታውቁ ይመስለኛል፡፡ ሆኖም ከስራ ብዛትና በቀላሉ ኢንተርኔት ከማግኘት ችግር የተነሳ ከጊዜ ወዲህ በላልበልሃ ላይ ብሎግ ማድረግ አቁሜያለው፡፡ በቅርቡም ለብሎጉ ጎብኚዎችና subscribers በይፋ በማሳወቅ ብሎጉን delete ለማድረግ አስቤያለው፡፡ ጽሁፎቹን ያላነበቡና በድጋሚ ለማንበብ የሚፈልጉ እንደሚኖሩ በመረዳት የተወሰኑትን Ethiopian Legal Brief ላይ አወጣቸዋለው፡፡
የሚከተሉት የችሎት ገጠመኞችና ቀልዶች ከፊሎቹ በላልበልሃ ላይ የወጡ ሲሆን የተቀሩት አዲስ ናቸው፡፡ የህግ ሰዎች! እስቲ ትንሽ ዘና እንበል፡፡
የችሎት ገጠመኞች
ቅርንጫፍ የሌለው ባንክ
ምስክሩ የምስክርነት ቃሉን በእውነት ለመስጠት ቃለ-መሃላ ፈጽሞ ከዳኛው ፊት ለፊት ተቀመጠ፡፡ ዳኛውም ስም ዕድሜ አድራሻ ከጠየቁት በኋላ ቀጣዩን ጥያቄ አቀረቡለት፡፡
ስራ?
ምስክር – ባንክ
ዳኛ – የትኛው ባንክ?
ምስክር – አይ አይደለም ጌታዬ! እኔ እቺ የቆርቆሮ ባንክ ነው የምሰራው፡፡
ቻርጅ እና ቻርጀር
በሞባይል ስልክ ስርቆት ተጠርጥሮ ክስ የቀረበበት አንድ ግለሰብ በቀጠሮው ቀን ፍርድ ቤት ሲቀርብ ዳኛው ‹‹ቻርጁ ደርሶሃል?›› ሲሉ ይጠይቁታል፡፡ ምን ያለበት ምን አይችልም እንዲሉ የዳኛውን ጥያቄ በወጉ ያልተረዳው ተከሳሽ “የምን ቻርጀር?” እኔ የወሰድኩት ሞባይል ብቻ ነው” በማለት ፈጣን ቃሉን ሰጥቷል፡፡
መከላከያ በችሎት
በአንድ ወቅት በወንጀል የተፈረደበት አንድ ደንበኛ ይግባኝ እንዳቀርብለት ጠይቆኝ ስለጉዳዩ የበለጠ ለመረዳት አንዳንድ ጥያቄዎች አቀረብኩለት፡፡ ትንሽ ማውራት እንጀመርን የተከሰሰበትን ድርጊት በበቂ ሁኔታ የሚያስተባብሉ የሰነድና የሰው ማስረጃ እንዳሉት ተረዳሁ፡፡ ይሁን እንጂ ፍርዱን ሳነበው ተከላከል የሚል ብይን ከተሰጠበት በኋላ መከላከያ እንዳለው ሲጠየቅ “የለኝም” ብሏል::
እኔም ይህ ሁሉ በቂ ማስረጃ እያለው ለምን መከላከያውን እንዳላቀረበ በጣም ተገርሜ መከላከያ እንዲያቀርብ ዕድል የተሰጠው መሆኑን ጠየቅኩት፡፡
እሱም “አዎ መከላከያ አለህ? ሲለኝ የለኝም” ብያለው
የባሰ በመገረም “ለምን?” ብዬ ጠየቅኩት::
“መከላከያ ሲል መከላከያ ሰራዊት መሰለኛ!”
የችሎት ቀልዶች
ተከሳሽ– “ክቡር ፍርድ ቤት ሌላ ተከላካይ ጠበቃ እንዲሾምልኝ እጠይቃለሁ::”
ዳኛ– “ምንድነው ምክንያትህ?”
ተከሳሽ– “ይሄኛው ተከላካይ ጠበቃ የኔን ጉዳይ ችላ ብሎታል፡፡
ዳኛ– ወደ ተከላካይ ጠበቃ ዞረው “እህ ለተከሳሹ ቅሬታ የምትለው ነገር አለህ?”
ተከላካይ ጠበቃ– “ኧ!? ምን አሉኝ? ይቅርታ ጌታዬ እየሰማሁ አልነበረም፡፡”
* * * * * * * * * *
ዳኛው ተከሳሹን “ፍርድ ቤት ተከላካይ ጠበቃ እንዲያቆምልህ ትፈልጋለህ?” ሲሉ ይጠይቁታል
ተከሳሽ –“አይ በራሴ ብከራከር እመርጣለሁ፡፡ የቀረበበኝ ክስ እኮ በጣም ከባድ ነው!”
* * * * * * * * * *
በአንድ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ክስ ዐቃቤ ህጉ ዳኛውን “ጌታዬ ይህ ድርጊት የተፈጸመው ተስተናጋጅ ጢም ብሎ በሞላበት ሬስቶራንት ውስጥ ነው፡፡” ብሎ መናገር ሲጀምር በነገሩ የተደመሙት ዳኛ “በእኔ ተሞክሮ ግን ይህን መሰል ድርጊቶች የሚፈጸሙት ተስተናጋጅ በሌለበትና ሬስቶራንቱ ዝግ በሚሆንበት ጊዜ ነው፡፡” ሲሉት ዐቃቤ ህጉ ነገረኛ ቢጤ ነበረና “አይ ጌታዬ! እኔ እንኳን እንደዛ ዐይነት ተሞክሮ የለኝም!” በማለት የተከበሩት ዳኛ ላይ አላግጦባቸዋል፡፡
* * * * * * * * * *
ዳኛው የተምታታ ክርክር እያቀረበ ሃሳቡ አልጨበጥ ያላቸውን ጠበቃ “ያንተን ክርክር ጭራውን እንኳን ለመያዝ አቅቶኛል፡፡ በአንዱ ጆሮ ገብቶ በሌላኛው ይወጣል” ይሉታል፡፡ ጠበቃውም የሚሸነፍ ዓይነት አልነበረምና “ጌታዬ በመሀል ሆኖ የሚያቆመው ነገር ምን አለ?” ሲል መልሶላቸዋል፡፡
* * * * * * * * * *
ከግራ ወደቀኝ እየተመላለሰ ባለማቋረጥ ለረጅም ጊዜ ክርክሩን በማቅረብ ላይ ያለ አንድ ሞቅ ያለው ጠበቃ በንግግሩ መሀል ቆም ብሎ “እየተከተሉኝ ነው ጌታዬ?” ሲል ዳኛውን ይጠይቃቸዋል፡፡ ዳኛውም “አዎ በቅርበት እተከተልኩህ ነው፡፡ ግን ግራ የገባኝ ነገር ወዴት ነው የምትሄደው?” በማለት መልሰው በነገር ጠቅ አድርገውታል፡፡
Filed under: law fun, Lawyers
