ሰበር ውሳኔ የሰጠበት ህግ ‘ሲሻር’ የውሳኔው የአስገዳጅነት ውጤት
የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ችሎት ውሳኔ በስር ፍርድ ቤቶች ላይ የአስገዳጅነት ውጤት እንዲኖረው በህግ የተደነገገው በ1997 ዓ.ም. ሲሆን የሰበር ችሎት የዚህን አዋጅ መውጣት ተከትሎ በሰበር ስልጣኑ የሚሰጣቸው ውሳኔዎች በፌደራልና በክልል የስር ፍርድ ቤቶች ላይ የአስገዳጅነት ውጤት አግኝተዋል፡፡ ሆኖም በአዋጅ ቁ 454/1997 ላይ የድንጋጌ ለውጥ ሳይኖር የአንድ አዋጅን መሻር ተከትሎ በሰበር ትርጉም የተሰጠበት ውሳኔ የሚኖረው ህጋዊ ውጤት በህጉ አፈፃፀም ላይ በተግባር የሚያጋጥም ችግር ሆኗል፡፡
በእርግጥ ሰበር ትርጉም የሰጠበት ህግ ተሸሮ ትርጉም የተሰጠበት ድንጋጌም ቀሪ ወይም ውጤት የሌለው በሚሆንበት ጊዜ ውሳኔውም ያለ አንዳች ቅድመ-ሁኔታ ለቀጣይ ተመሳሳይ ጉዳዮች የአስገዳጅነት ውጤት ሊኖረው እንደማይችል ግልጽ ነው፡፡ ለምሳሌ አዋጅ ቁጥር 639/2001 ለባንክ ወይም ለአነስተኛ የፋይናንስ ተቋም ብድር መያዣነት የተሰጠ የማይንቀሳቀስ ንብረትን የሚመለከት ውል በፍርድ ቤት መዝገብ ወይም ስልጣን በተሰጠው አዋዋይ ፊት መፈረም እንደማያስፈልገው በመደንገግ በፍትሐ ብሔር ህግ ቁጥር 1723 ስር የተመለከተውን ቅድመ-ሁኔታ በከፊል ቀሪ አድርጎታል፡፡ ስለሆነም የሰበር ችሎት ከዚህ አዋጅ መውጣት በፊት የፍትሐ ብሔር ህግ ቁጥር 1723ን መሰረት በማድረግ ለባንክ ወይም ለአነስተኛ የፋይናንስ ተቋም ብድር መያዣነት የተሰጠ የማይንቀሳቀስ ንብረትን የሚመለከት ውልን በመተርጎም የሰጣቸው ውሳኔዎች በስር ፍርድ ቤቶች የአስገዳጅነት ውጤት አይኖራቸውም ማለት ነው፡፡
ይሁን እንጂ አንዳንድ ጊዜ አንድ አዋጅ ሙሉ በሙሉ ተሽሮ በአዲስ አዋጅ ሲተካ በተሻረው አዋጅና በአዲሱ አዋጅ የሚገኙ የተወሰኑ ድንጋጌዎች ምንም ዓይነት የይዘት ለውጥ አይደረግባቸውም፡፡ ለዚህ ጥሩ አብነት የሚሆነን የአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁጥር 42/85 በ377/96 መተካት ነው፡፡ ምንም እንኳን አዋጅ ቁጥር 42/85 በ377/96 የተሻረ ቢሆንም በቀድሞው አዋጅ ላይ የነበሩ ብዙ ድንጋጌዎች ምንም ዓይነት የይዘት ለውጥ አልተደረገባቸውም፡፡ ለምሳሌ የአዋጁን የተፈጻሚነት ወሰን የሚመለቱ ድንጋጌዎች፤ የስራ ውል አመሰራረትን የሚመለከቱ ድንጋጌዎች፤ የስራ ውል የሚቆይበትን ጊዜ አስመልክቶ የተቀመጡ ድንጋጌዎች (አዲስ ንዑስ አንቀጾች ከመጨመራቸው ውጪ የቀድሞ ድንጋጌዎች አልተቀየሩም) እንዲሁም ሌሎች ብዙ ድንጋጌዎች ይዘታቸው አልተቀየረም፡፡
እዚህ ላይ ጥያቄ ይነሳል፡፡ የይዘት ለውጥ ባልተደረገበት አንቀጽ ላይ አዋጅ ቁጥር 42/85ን መሰረት በማድረግ በሰበር የተሰጠ ውሳኔ አዋጁ በ377/96 ከተሻረ በኋላም የአስገዳጅነት ውጤት አለው?
በዚህ ነጥብ ላይ የሰበር ችሎት በሁሉም ዓይነት የስራ ክርክር፤ የፍትሐብሔር፤ የወንጀልና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ወጥ በሆነ መልኩ ተፈፃሚነት ያለው ውሳኔ ያልሰጠ ቢሆንም የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይን በተመለከተ ግን በከፊልም ቢሆን ምላሽ ሰጥቶበታል፡፡ ስለሆነም በአዋጅ ቁጥር 42/85 መሰረት የተሰጠ የሰበር ውሳኔ አዋጅ ቁጥር 377/96 ከወጣ በኃላ በአዲሱ አዋጅ መሰረት የሚነሱ የስራ ክርክሮች ላይ የሚኖረውን ህጋዊ ውጤት በከፊልም ቢሆን ምላሽ ያገኘ ይመስላል፡፡
በሐመረ ወርቅ ቅ/ማሪያም ቤተክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤት እና እነ ዲያቆን ምህረተ ብርሐን (6 ሰዎች) (የሰ.መ.ቁ.18419 ግንቦት 4 ቀን 1998 ዓ.ም) በነበረው የአሰሪና ሰራተኛ ክርክር ሰበር ችሎቱ የተያዘውን ጉዳይ ብቻ አስመልክቶ እንዳለው አዋጅ ቁጥር 42/85 በአዋጅ ቁጥር 377/96 የተሻረ ቢሆንም ነጥቡን በሚመለከት ሁለቱ አዋጆች አንድ አይነት ድንጋጌዎችን የያዙ በመሆኑ ችሎቱ የአዋጅ ቁጥር 42/85 ድንጋጌዎችን መሰረት አድርጎ በተጠቀሰው ነጥብ ላይ የሰጠው የህግ ትርጉም ለአዋጅ ቁጥር 377/96 ድንጋጌዎችም አግባብነት ያለው ነው፡፡
Filed under: Articles, Case Comment, Employment law
