ዳኞች በተሻረ ህግ ውሳኔ ሰጥተዋል የሚባለው የጭምጭምታ ወሬ ከተራ ሐሜት ወደ ቁንጽል እውነት የመሸጋገሩ ነገር ከተገቢ ጥርጣሬ በላይ ባይረጋገጥም በአዲስ አዋጅ መዘግየት ምክንያት ፈጣን ፍትህ ለመስጠት መቸገራቸው ግን ገሃድ የወጣ ሐቅ ነው፡፡ አልፎ አልፎ የሚያጋጥም ቢሆንም ክስተቱ የአገሪቱን የህግ ሥርዓትና የህግ የበላይነት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ጥቁር ነጥብ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ አዲስ የወጣ ህግ እንዲደርሳቸው የሚገባው ፍርድ ቤቶች ቢሆኑም እዛም ቤት ችግር መኖሩ የችግሩን ስፋትና ጥልቀት ይጠቁመናል፡፡ በተለይ ከአዲስ አበባ ውጭ ርቀው የሚገኙ ፍርድ ቤቶች አዲስ የወጣ አዋጅ በየጊዜው ስላልደረሳቸው ብቻ የመውጣቱን ዜና በጥቅሉ ከሚዲያ ሰምተው ለዚሁ ሲባል የያዙትን ጉዳይ ለሌላ ቀጠሮ ማስተላለፋቸው ለማስተዋል ተችሏል፡፡
ግልጽነት በኢ.ፌ.ድ.ሪ. ህገ-መንግስት እንደ መሰረታዊ መርህ ቢቀመጥም እውነታው ግን በወረቀት ከተፃፈው ጋር ሊጣጣም አልቻለም፡፡ የመንግስት አስተዳደርን በተመለከተ የዜጋው መረጃ የማግኘት መብት እስከአሁን ድረስ በተግባር አልተረጋገጠም፡፡ እዚህ ላይ ለመድረስ ገና ብዙ የሚቀረን ነው የሚመስለው፡፡ ይህን ለመረዳት ብዙ ርቆ መሄድ አያስፈልግም፡፡ እንኳንስ ከመንግስት መስሪያ ቤት መረጃና ሰነድ ማግኘት ቀርቶ የግድ የሚለውን የአገሪቱን ህጎች በቀላሉ ለማግኘት አስቸጋሪ የሆነበት ደረጃ ላይ ደርሰናል፡፡
አዋጅ፤ ደንብና መመሪያ በአነስተኛ ወጪ በቀላል መንገድ ለዜጋው የማይደርሱ ከሆነ የህጉን ብቃት ብቻ ሳይሆን የህግ የበላይነትን ጥያቄ ውስጥ ያስገባል፡፡ በተወካዮች ምክር ቤት የሚወጣ አዋጅ እና በውክልና ስልጣን በሚኒስትሮች ምክር ቤት የሚወጣ ደንብ በነጋሪት ጋዜጣ መውጣት እንዳለበት በአዋጅ ቁጥር 3/1987 የተደነገገ ሲሆን በዚሁ መሰረት ሁለቱም በነጋሪት ጋዜጣ ይታተማሉ፡፡ ይሁን እንጂ በተለያዩ የአስተዳደር መስሪያ ቤቶች የሚወጡ መመሪያዎች እንዲታተሙ አስገዳጅ ህግ ባለመኖሩ ምክንያት ዜጌች ለማያውቁት መመሪያ እንዲገዙ ተደርገዋል፡፡
በተጨማሪም አዋጆችና ደንቦች በፌደራል ነጋሪት ጋዜጣ መታተማቸው ብቻ የህዝቡን ህግን የማወቅ መብትና ግዴታ በተመለከተ ያለውና ችግር ሊፈታው አልቻለም፡፡ የህጎች መታተም (Publication of laws) ሲባል አዋጅ፣ ደንብ፣ መመሪያ ለህዝቡ በአነስተኛ ወጪ በቀላሉ ሊደርስ በሚችል የህትመት ውጤት ላይ ታትመው መውጣታቸው ብቻ ሳይሆን ለህዝቡ ተደራሽ በሆነ መልኩ ማሰራጨትንም (Distribution) ይጨምራል፡፡ አንድ ህብረተሰብ ላልታተመና ቢታተምም በቀላሉ ለማይገኝ ህግ ሊገዛ አይችልም፡፡ ህግን አለማወቅ ይቅርታ ባያሰጥም የዚህ መርህ መሰረቱ ህጉ በቀላሉ መገኘት መቻሉ ነው፡:
በፌደራል ነጋሪት ጋዜጣ የሚታተሙ አዋጆችና ደንቦች ለህዝቡ የሚደርሱት በሽያጭ ሲሆን በሁሉም ክልሎች ለሚኖረው ዜጋ ያለው የመሸጫ ቦታ አንድ ብቻ ማለትም በአዲስ አበባ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት የሽያጭ ማዕከል ብቻ ነው፡፡ (ማተሚያ ቤቱ በልደታ ፍርድ ቤት ውስጥ አንድ ተጨማሪ የሽያጭ ማዕከል ቢኖረውም አብዛኛውን ጊዜ ጠይቃችሁ የምታገኙት ምላሽ “የለም” የሚል ነው፡፡ ስለሆነም የሽያጭ ማዕከሉም የለም ቢባል ይሻላል::) ይህ ሁኔታ በተለይ ከአዲስ አበባ ርቆ ለሚገኝ ህግን አውቆ ለህጉ መገዛት ለሚፈልግ ዜጋ የሚፈጥረውን ችግር ሁሉም የሚገምተው ብቻ ሳይሆን በተጨባጭ የሚያየው አሁንም ያልተቀረፈ ስህተት ድክመትና ግድፈት ነው፡፡ ለዚህም ህግ አውጪው አካል ኃላፊነትና ተጠያቂነቱን ሊሸከም ይገባል፡፡
የችግሩ ተጋሪ የህግ እውቀት የሌለው ዜጋ ብቻ አይደለም፡፡ ዳኞች፣ ጠበቆች፣ ነገረ-ፈጆች የህግ ባለሙያዎች እንዲሁም ከአዲስ አበባ ርቀው የሚገኙ የመንግስት መስሪያ ቤቶች፤ የመንግስት የልማትና የግል ድርጅቶች ሁሉም በየፈርጁ የችግሩ ተጋሪዎች ናቸው፡፡ ይህም አንድን የአስተዳደር ውሳኔ፣ ድርጊት ወይም እርምጃ በህጉ መሰረት አይደለም ብሎ ጥያቄ ለማንሳትና መብት ለማስከበር አስቸጋሪ አድርጎታል፡፡ የችግሩ መኖር ለሌላ ጠባሳ በር በመክፈት የበዘፈቀደ አሰራር፣ ከስልጣን በላይ የሆነ ድርጊት እና የስልጣን አለአግባብ መገልገል እንዲበራከትና ዜጎች በአስተዳደር በደል የተነሳ መብታቸው እንዲጣስ ትልቁ ምክንያት ሆኗል፡፡ የአንድ አገር ህጎች ተደራሽ ባልሆኑበት ሁኔታ አስተዳደሩ ስራውን በህጉ መሰረት እንዲያከናውን፤ ህጋዊነትን ካልተከተለም በህግ እንዲጠየቅ ይህም ማለት የህግ የበላይነት እንዲሰፍንና እንዲከበር ለማድረግ የሚታለም እንኳን ቢሆን የሚተገበርና በተጨባጭ የሚረጋግጥ ግን አይሆንም፡፡
የነጋሪት ጋዜጣ መሸጫ ዋጋ እንዲሁ ኑሮ ለከበደው ዜጋ የሚቀመስ አይደለም፡፡ በአሁኑ ወቅት ሁለት ገጽ ነጋሪት ጋዜጣ በሁለት ብር ከሰላሳ ሳንቲም ይቸበቸባል፡፡ የነጋሪት ጋዜጣ ሽያጭ ከአዋጭነቱ አንፃር ሳይሆን ከዜጎች ህግን የማወቅ መብትና ለህጉ ተገዢ እንዲሆኑ የማድረግ ግዴታ ጋር ተዛምዶ ሊታይ ይገባዋል፡፡ ከማንም በላይ የጉዳዩ ባለቤት የሆነው የተወካዮች ምክር ቤት የህትመቱንና የሽያጩን ስራ በሞኖፖል ተቆጣጥሮት ከሚገኘው የብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት በመረከብ ከዋጋ ትመናው አንስቶ የህትመት ስርዓቱን፤ ሽያጩንና ስርጭቱን ራሱ በሚያቋቁመው ማተሚያ ቤት ስር ሆኖ እንዲከናወን የማድረግ ትልቅ ግዴታ ተጥሎበታል፡፡ ይህ ሲሆን ብቻ ነው በስርቻው ስር ተደብቀው የሚገኙት ህጎች ብርሃን የሚወጣላቸው፡፡
ምክር ቤቱ የህትመት ስርዓቱን በራሱ ማተሚያ ቤት እንዲሆን ማድረጉ የህጎችን ህትመትና ስርጭት ውጤታማ ከማድረግ ባለፈ አንዳንዴ ከሚፈጠሩ አስደንጋጭ ስህተቶችም ነጻ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ በዚህ ረገድ የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደርን ለማቋቋም የወጣው አዋጅ ቁጥር 510/1999 እና የተሻሻለው የአዲስ አበባ ከተማ ቻርተር አዋጅ ቁጥር 311/1995 የተሻሩበት ምክንያት ጥሩ አስረጂ ሊሆነን ይቸላል፡፡
አዋጅ ቁጥር 510/1999ን የሻረው የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደርን እንደገና ለማቋቋም የወጣ አዋጅ ቁጥር 535/1999 አንቀጽ 22(1) እንዲህ ይነበባል፡፡
“ምክርቤቱ ባጸደቀው መልኩ ያልወጣ በመሆኑ የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደርን ለማቋቋም የወጣው አዋጅ ቁጥር 510/1999 በዚህ አዋጅ ተሸሯል፡፡”
በተመሳሳይ መልኩ አዋጅ ቁጥር 311/1995 በተሻሻለው የአዲስ አበባ ከተማ ቻርተር አዋጅ ቁጥር 361/1995 ሲሰረዝ በአንቀጽ 67(1) ላይ የቀረበው ምክንያት የሚከተለው ነበር::
“የህግ አወጣጡን ስነ-ስርዓት ባልተከተለ አኳኋን የይዘት ለውጥ ተደርጎበት የታተመ በመሆኑ፤ የተሻሻለው የአዲስ አበባ ከተማ ቻርተር አዋጅ ቁጥር 311/1995 ተሰርዞ በዚህ አዋጅ ተተክቷል፡፡”
ተመሳሳይ ስህተቶች እንይፈጠሩ ብሎም ህጎች በቀላሉ ለዜጋው ተደራሽ ይሆኑ ዘንድ ምክር ቤቱ የራሱ ማተሚያ ቤት እንዲኖረው አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን የግድ ነው፡፡
ህጎችን ለማግኘት አለመቻል በተለይም በመመሪያዎች ላይ አንገብጋቢና ስር የሰደደ ችግር ሆኗል፡፡ በአገራችን በአስተዳደር መስሪያ ቤቶች የሚወጡ መመሪያዎች በየትኛውም ዓይነት የህትመት ውጤት ታትመው እንዲወጡ የሚያስገድድ ህግ የለም፡፡ ማንኛውም መመሪያ የሚወጣው የተወካዮች ምክር ቤት የህግ አውጭነት ስልጣኑን በከፊል ቆርሶ በህዝብ ላልተመረጡ የአስተዳደር አካላት በውክልና ስልጣን ሲሰጣቸው ነው፡፡ ከውክልና ስልጣን ገደብ በላይ የወጣ መመሪያ ህገ-ወጥ ነው፡፡ በህዝብ የተመረጠ አካል ከህዝብ ያገኘውን ህግ የማውጣት ስልጣን በከፊል በህዝብ ላልተመረጠ አካል በውክልና ሲያስተላልፍ ይህ ስልጣን በአግባቡ የህጉን ዓላማ ለማስፈፀም ብቻ መዋሉንና ለህዝቡም በቀላሉ መድረሱን የማረጋገጥ አደራ ኃላፊነትና ግዴታ ተጥሎበታል፡፡
በተግባር እንደምናየው የመንግስት ባለስልጣንና ሰራተኛ ስራውን የሚያከናውነው በ”መመሪያው መሰረት” ነው፡፡ ዜጎች “መመሪያው አይፈቅድም” በሚል መብትና ጥቅማቸውን በእጅጉ የሚጎዳ የአስተዳደር ውሳኔ እና እርምጃ ይወሰድባቸዋል፡፡ የተባለው መመሪያ በእርግጥ ይኑር አይኑር ለዚህ ዜጋ ፈጽሞ የሚታወቅ አይደለም፡፡ መመሪያው አንዳንዴ ከአስፈጻሚው መስሪያ ቤት ከራሱ የተሰወረ የሚሆንበት አጋጣሚ ይፈጠራል፡፡ የመመሪያውን ይዘት በራሱ አንብቦ ወይም ለተማረ ጎረቤቱ አስነብቦ ለመረዳትና መብቱን ለማስከበር የሚፈልግ ሰው መመሪያው እንዲሰጠው ቢጠይቅ መመሪያው “ከቢሮ አይወጣም” ወይም መመሪያው “ሚስጥራዊ ነው” የሚል ራስ የሚያሳምም አስገራሚ ምላሽ ይሰጠዋል፡፡
እዚህ ላይ የሰበር ውሳኔዎች ተደራሽነት ችግርም ትኩረት የሚሻ ጉዳይ ሆኗል፡፡ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከአምስት ያላነሱ ዳኞች በተሰየሙበት የሰበር ችሎት የሚሰጠው የህግ ትርጉም በየትኛውም ደረጃ ላይ በሚገኝ የፌደራል ወይም የክልል ፍርድ ቤት ላይ አስገዳጅነት እንዲኖረው በህግ (የፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅን እንደገና ለማሻሻል የወጣ አዋጅ ቁጥር 454/1997) ከተወሰነ አስር ዓመታት ገደማ አስቆጥሯል፡፡ በአዋጅ ቁጥር 454/1997 አንቀጽ 2(5) እንደተመለከተው የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አስገዳጅ የህግ ትርጉም የተሰጠባቸውን ውሳኔዎች በየደረጃው ላሉ ፍርድ ቤቶችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት አሳትሞ እንዲያሰራጭ ግዴታ ተጥሎበታል፡፡ በዚህ መልኩ አስራ አምስት ቅጾች ታትመው ተሰራጭተዋል፡፡ ሆኖም ህትመቱና ስርጭቱ በትንሹ አመት እንዲጠብቅ መደረጉ ተደራሽነቱን ከጊዜ አንጻር ወደኋላ እንዲጎተት አድርጎታል፡፡ ህትመትና ስርጭቱን ቢቻል ሳምንታዊ ካልተቻለም ወርሀዊ ለማድረግ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ለምን እንደከበደው ከፍርድ ቤቱ ከራሱ ምላሽ የሚፈልግ ጥያቄ ነው፡፡
ከቅጾቹ ህጋዊ ውጤት ጋር በተያያዘም ተዛማጅ ጥያቆዎች መነሳታቸው አይቀሬ ነው፡፡ ለምሳሌ የሰበር ችሎት በዛሬው ቀን በህግ ትርጉም ላይ የሰጠው ውሳኔ የአስገዳጅነት ውጤት የሚኖረው ከመቼ ጀምሮ ነው? ውሳኔው ከተሰጠበት (በግልጽ ችሎት ከተነበበት)? ውሳኔው በኮምፒዩተር ተጽፎና ተመሳክሮ በሬጅስትራሩ ማህተም ከተደረገበት? ወይስ በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር ውሳኔዎች ቅጽ ላይ ታትሞ ከወጣበት? በአጠቃላይ በሰበር የሚሰጡ ውሳኔዎች በቅጽ ተዘጋጅተው እስኪታተሙ ድረስ የሚኖራቸው የአስገዳጅነት ውጤት ራሱን የቻለ የህግ ትርጉም የሚሻ ጉዳይ ነው፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ በቅጾቹ ላይ ያልተካተቱ የሰበር ውሳኔዎች የአስገዳጅነት ውጤትም ቁርጥ ያለ ምላሽ ያገኘ አይደለም፡፡ እስካሁን በወጡት አስራ አምስት የሰበር ውሳኔዎች ላይ ያልተካተቱ የሰበር ውሳኔዎች የመኖራቸው ጉዳይ እርግጥ ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ውሳኔዎች ስለመኖራቸው እርግጠኛ ሆኜ መናገር ብችልም በስር ፍርድ ቤቶች ላይ ስላላቸው የአስገዳጅነት ውጤት ግን እርግጠኛ ሆኜ መናገር አልችልም፡፡
የቅጾቹ ስርጭት ስፋት በአዋጁ አንቀጽ 2(5) ላይ በየደረጃው ላሉ “ፍርድ ቤቶችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት” በሚል ተገድቧል፡፡ ይሁን እንጂ በሰበር የተሰጠ የህግ ትርጉም ከፍርድ ቤቶችና ከሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ባለፈ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ይመለከታል፡፡ በሰበር የሚሰጥ ትርጉም ምንም እንኳን አስገዳጅነቱ “በየትኛውም ደረጃ ላይ በሚገኝ የፌደራል ወይም የክልል ፍርድ ቤት ላይ” በሚል ገዳቢ ሐረግ የታሰረ ቢሆንም ውጤቱ ግን ከዚህ እጅግ በሰፋ መልኩ በሁሉም የአገሪቱ ዜጋና ከዛም አልፎ በአገሪቱ ውስጥ በሚገኝ የውጭ አገር ዜጋና ድርጅት ጭምር ላይ ነው፡፡ ስለሆነም የተወካዮች ምክር ቤት ከሚያወጣው አዋጅ ሆነ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ከሚያወጣው ደንብ ተለይቶ መታየት የለበትም፡፡ ህትመቱና ስርጭቱ ለሁሉም ዜጋ በአነስተኛ ወጪ በቀላሉ እንዲደርስ ካልተደረገ የአገሪቱን የህጎች ተደራሽነት ጥያቄ ጥያቄ ውስጥ ይከተዋል፡፡
እንግሊዝ አገር ውስጥ በነበረ አንድ የአስተዳደር ክርክር ላይ ውሳኔውን የሰጡት ዳኛ እንዲህ ብለው ነበር፡፡
‹‹ህግን አለማወቅ ይቅርታ አያሰጥም የሚለው መርህ በእንግሊዝ ዲሞክራሲ የህግ የበላይነት የቆመበትን መሪ ሀሳብ ይወክላል፡፡ ነገር ግን የዚህ መርህ የትክክኛነቱ መሰረት ሁሉም ህጎች በቀላሉ ለህዝቡ እንደሚደርሱ ግምት በመውሰድ ነው፡፡
በእርግጥ ህግን አለማወቅ ይቅርታ አያሰጥም፡፡ ግን ህግን አለማሳወቅም እንዲሁ ይቅርታ አያሰጥም፡፡ ህግ ህዝብና መንግስትን የየሚያገኛኝ ድልድይ ነው፡፡ ህግ ከህዝቡ ሲርቅ ህዝብ ከህግ ይርቃል፡፡ መንግስት ከህግ ይርቃል፡፡ መንግስትና ህዝብ ይራራቃሉ፡፡ የህግ የበላይነት ለሰዎች የበላይነት ቦታውን ያስረክባል፡፡ የሰዎች የበላይነት ከሚጀመርበት ቦታ ህገ-ወጥነት አፍታም ሳይቆይ ደግሞ ኢ-ህገ መንግስታዊነት ይከተላል፡፡
ሌላ ጥቅስ እናክልና እናብቃ፡፡ ኤድመንድ በርክ እንዲህ ብሎ ነበር፡፡
‹‹በአንድ ወቅት አንድ መልካም ሰው ሚስጥር ከሚጀምርበት ቦታ የሃይማኖት ፍፃሜ ይሆናል›› ብሎ ነበር፡፡ ለመሆኑ እኔስ ስለሰው ልጅ ህጎች “ሚስጥር ከሚጀመርበት ቦታ የፍትህ መጨረሻ ይሆናል” ብል እሳሳት ይሆን?››
Filed under: Articles
